በክልሉ በጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ተችሏል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ በጤና ተቋማት በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋት ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት ተችሏል
ባህር ዳር፤ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡-በአማራ ክልል የጤና ተቋማትን አገልግሎት አሰጣጥ በቴክኖሎጂ የታገዘ በማድረግ ለማህበረሰቡ የተሻለ አገልግሎት መስጠት መቻሉን የክልሉ ጤና ቢሮ ገለፀ።
የቢሮው የ2018 ዕቅድ አፈፃፀምና የ2019 ዕቅድ ዙሪያ የሚመክር መድረክ በባህር ዳር ከተማተካሂዷል።
የቢሮው ሃላፊ አቶ አብዱልከሪም መንግስቱ በመድረኩ ላይ እንዳሉት፤ በክልሉ የጤና አገልግሎት አሰጣጡን በማዘመን በኩል ውጤታማ ተግባራት ተከናውነዋል።
በዚህም ዘላቂና የተደራጀ የጤና ስርዓት በመገንባት የተቋማትን የአገልግሎት አሰጣጥ ማዘመን እየተቻለ መሆኑን ጠቁመው በህክምና ተቋማት ህሙማን ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኙ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
የጤና ተቋማትን በቴክኖሎጂ በማስተሳሰር እና ከወረቀት ነፃ አሰራርን በመዘርጋት የተገልጋዩን እንግልት የመቀነስ ስራም በትኩረት መከናወኑን አንስተዋል።
በየደረጃው በሚገኙ የህክምና ተቋማት ዘመኑ ያፈራቸውን የህክምና መሳሪያዎችን በማሟላት ማህበረሰቡን በአቅራቢያው መሰረታዊ የጤና ህክምና የአገልግሎት ተጠቃሚ በማድረግ የተሻለ ስራ መሰራቱን ተናግረዋል።
ዘላቂ የጤና ፋይናንስ ስርዓት በመገንባትም ሃብት መሰብሰብ እንደተቻለና በዚህም የህክምና አገልግሎቱን በራስ አቅም የመስጠት ሂደትን የማጠናከር ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በየደረጃው 109 የማህበረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በማቋቋም የማህበረሰቡን ተጠቃሚነት የማሳደግ ስራ መሰራቱን ጠቅሰዋል።
በ2019 በጀት ዓመት በሁሉም መስክ የተሻለ ስራ ለመስራት ታቅዶ እየተተገበረ መሆኑን አስታውቀዋል።
የክልሉ የማህበራዊ ክላስተር ፅህፈት ቤት ሃላፊ አቶ አባይ መላኩ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሽታዎችን ከመከላከል ባለፈ አክሞ የማዳን አቅም እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል።
የማህብረሰብ መድሃኒት ቤቶችን በመገንባት የመድሃኒት አቅርቦት እጥረትን ለመፍታት እና ለህክምና የተመቹ ፅዱና ማራኪ የጤና ተቋማትን በማስፋት በኩልም አበረታች ስራ መሰራቱን ገልፀዋል።
እንዲሁም ተቋሙ እያካሄደ ያለው የሪፎርም ስራ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት እየተከናወነ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
በጤናው ዘርፍ የተገኙ ውጤቶችን በማጠናከርም የማህበረሰቡን የጤና ችግር በመሰረታዊነት መፍታት እስኪቻል ድረስ የቅንጅት ስራዎች ተጠናክረው መቀጠል እንዳለባቸው አሳስበዋል።
በመድረኩ የክልልና በየደረጃው የሚገኙ የዘርፉ አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ባለድርሻ አካላት ተሳትፈዋል።