ቀጥታ፡

በክልሉ ለአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስኬታማነት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር ይገባል - ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ

‎ጋምቤላ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ በክልሉ እየተካሄደ ላለው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስኬታማነት የህብረተሰቡ ተሳትፎ ሊጠናከር እንደሚገባ የጋምቤላ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አለሚቱ ኡሞድ ገለፁ።

‎‎''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሀሳብ በክልሉ የ2018 የአረንጓዴ ዐሻራ መርሀ ግብር ማስጀመሪያ ስነ ስርአት በማጃንግ ዞን በመንገሺ ወረዳ ተካሂዷል።‎




ርዕሰ መስተዳድሯ በወቅቱ እንዳሉት የተፈጥሮ ሃብት ልማትና ጥበቃ ስራዎችን በማጠናከር ለግብርና ልማቱ ስኬታማነት ልንተጋ ይገባል።

‎በክልሉ የማይበገር የአረንጓዴ ኢኮኖሚ ልማትን ለማረጋገጥ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ስራዎች በርካታ ስኬቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።




ባለፉት የለውጥ አመታት በተከናወኑት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት በርካታ የተራቆቱ አካባቢዎች ከማገገማቸው ባለፈ የግብርና ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ማስቻሉን ገልፀዋል።

‎በቀጣይም የተጀመረውን ልማት በማሳለጥ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ ለተያዘው ግብ መሳካት ያላሰለሰ ጥረት ልናደርግ ይገባል ብለዋል።

‎በዘንድሮው ዓመት እየተከናወነ ላለው የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የክልሉ ህዝብ ተሳትፎና ትብብር ሊጠናከር እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሯ አሳስበዋል።




‎የክልሉ እርሻና ተፈጥሮ ሃብት ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ኡጁሉ ኡሞድ በበኩላቸው እንደገለጹት የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት የአየር ንብረት ለውጥ ተጋላጭነት በመቀነስና የአፈር ለምነትን በመጨመር የአርሶና አርብቶ አደሩን ምርታማነት በማሳደግ ረገድ የማይተካ ሚና አበርክቷል።

‎በክልሉ ባለፉት አመታት በተከናወኑ የአረንጓዴ ዐሻራ ልማት ከ50 ሺህ ሄክታር በላይ የተራቆተ መሬት በደን መሸፈኑን ጠቅሰዋል።

‎በአረንጓዴ ሻራ ልማት የለሙ የፍራፍሬና ሌሎች ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው ችግኞች በህብረተሰቡ ህይወት ላይ አወንታዊ ለውጥ እያመጡ መሆናቸውን ገልፀዋል።

‎ዘንድሮም ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶ የሚሆኑት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ያላቸው የፍራፍሬ ችግኞች መሆናቸውን አስታውቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም