መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ መከላከያ ሠራዊት የኢትዮጵያን ዕድገት የማይፈልጉ የጥፋት ኃይሎችን ተልዕኮ በማምከን ግዳጁን በአስተማማኝ ብቃት እየተወጣ እንደሚገኝ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ ያሰለጠናቸውን 71ኛ ዙር መተማ ኮርስ ዕጩ መኮንኖች እያስመረቀ ይገኛል።
በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን፣ የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዲየር ጄኔራል ጌታቸው ሃብታሙ፣ ጄኔራል መኮንኖችና የሀገራት ወታደራዊ አታሼዎች ተገኝተዋል።
የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ በምስራቅ አፍሪካ ቀጣና ባላት የጂኦ ፖለቲካ አቀማመጥና በተፈጥሮ ሃብቷ ምክንያት ለተለያዩ ፈተናዎች ስትጋለጥ የቆየች ሀገር ናት።
አርበኞች በታሪክ የሀገራቸውን ህልውና በመጠበቅ የተጫወቱትን ሚና በማስታወስ፤ በአሁኑ ወቅት የሀገርን ሰላምና ደኅንነት ለመፈታተን የሚሞክሩ ኃይሎች መኖራቸውን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በልማትና በብልፅግና ጉዞ ላይ መሆኗን የማይወዱ የጥፋት ኃይሎች ሴራና ደባ ለመፈጸም እየሞከሩ መሆኑንም ገልጸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሀገር ፍቅር፣ በአርበኝነትና ሕዝብን የማገልገል ዕሴቶች በመላበስ ኢትዮጵያን ለማዳከም የሚቃጡ የጥፋት ሴራዎችን በብቃት እያመከነ መሆኑን ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ የሚገጥማትን ፈተና በድል ለመወጣት ከትውልድ ትውልድ የተላለፈ የወል ብቃት ያላት ሀገር መሆኗን በመጥቀስ።
ይሁንና ዘመኑ የሚጠይቀውን የደኅንነት ፈተና ለመመከት የወል ብቃት ብቻ በቂ እንደማይሆን ጠቅሰው፤ ያለውን አቅም በሰው ኃይል ልማት፣ በትምህርትና በዘመናዊ ቴክኖሎጂ ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልጸዋል።
በዚህም የመከላከያ ሠራዊት የማሰልጠንና የማብቃት ተልዕኮውን በማጠናከር በርካታ የስልጠና ተቋማትን በማስፋፋት የሰው ኃይል ልማት ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን አብራርተዋል።
በዚህም የሠራዊቱ የሙያ ብቃት፣ የዘመናዊ ቴክኖሎጂ አጠቃቀምና የተልዕኮ አፈጻጸም አቅም እየጎለበተና እየዘመነ መምጣቱን ጠቁመዋል።
የመከላከያ ትምህርትና ሥልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄኔራል ይመር መኮንን በበኩላቸው፤ ዘመናዊ ሠራዊት ግንባታን እውን ማድረግ የሚያስችሉ የትምህርትና ስልጠና ማዕከላት ተገንብተዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚና ሌሎች የሥልጠና ማዕከላት ዘመኑን የዋጀ ሥርዓተ ትምህርት በመቅረፅ በቴክኖሎጂ፣ በአስተሳሰብ፣ በአሰራር የበቁ የሠራዊትና አመራር አባላት እየተፈጠሩ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ በዛሬው ዕለት ያስመረቃቸው የ71ኛ መተማ ካዴት ዕጩ መኮንኖችም የዚህ ጥረት መገለጫዎች መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
የኢትዮጵያ ወታደራዊ አካዳሚ አዛዥ ብርጋዴር ጄኔራል ጌታቸው ሀብታሙ፤ ተመራቂዎቹ የወሰዱት ስልጠና ሁለንተናዊ የአመራር ጥንካሬን የሚያጎለብት መሆኑን ገልጸዋል።
ዕጩ መኮንኖቹ ያገኙት ትምህርትና ስልጠና ማንኛውንም የሠራዊት የግዳጅ ተልዕኮ መወጣት የሚያስችል አቅም አጎናፅፏቸዋል ብለዋል።
ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት አባላት በተጨማሪ ከተለያዩ ሀገራት የመጡ አፍሪካውያን ዕጩ መኮንኖችም ስልጠናቸውን አጠናቀው መመረቃቸውን ተናግረዋል።