የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ትሩፋትና የሕብረብሔራዊ አንድነት የልማት ምልክት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የአረንጓዴ ዐሻራ የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ትሩፋትና የሕብረብሔራዊ አንድነት የልማት ምልክት ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ የአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር የኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ ትሩፋትና የሕብረብሔራዊ አንድነት የልማት ምልክት መሆኑን በጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርአት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትር ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) ገለጹ።
የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት (ኢዜአ) አመራር አባላት በኦሮሚያ ክልል ቢሾፍቱ ከተማ ሆራ አርሰዲ ሐይቅ ዳርቻ ''ተስፋን እንትከል'' በሚል መሪ ሃሳብ የአረንጓዴ ዐሻራቸውን አኑረዋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ማዕከል አስተባባሪ ሚኒስትርና የኢዜአ ቦርድ ሰብሳቢ ቢቂላ ሁሪሳ (ዶ/ር) እንዳሉት፤ አረንጓዴ ዐሻራ በዓለም አደባባይ የኢትዮጵያን ስምና ዝና ከፍ እያደረገ የሚገኝ ሀገራዊ ተነሳሽነት ነው።
በሀገራዊ ለውጡ ማግስት በኢትዮጵያ በርካታ ቢሊየን ችግኞች መተከላቸው ሀገር ወደ አረንጓዴ ኢኮኖሚ የምታደርገው ሽግግር እየሰመረ መሆኑን በተግባር እንደሚያሳይ ገልጸዋል።
አረንጓዴ ዐሻራ ከሀገር ውስጥ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ ባሻገር በቀጣናዊ ትብብር ውስጥም አዲስ የዲፕሎማሲ መልዕክት እያስተላለፈ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት ችግኝ በማቅረብና የአካባቢ ጥበቃ ተሞክሮዎችን በማካፈል ቀጣናዊ ትስስርን እያጠናከረች ነው፤ ይህም በርካታ የዲፕሎማሲ ትሩፋቶችን እያስገኘ ነው ብለዋል።
የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም የወሰድነው ተግባራዊ እርምጃ ዓለም እንደ ተሞክሮ እየተመለከተው መሆኑንም ጠቅሰዋል።
ይህም ኢትዮጵያ ዓለም አቀፍ ዕውቅናና አድናቆት እንድታገኝ እንዳስቻላት አብራርተዋል።
በሀገር ውስጥም አረንጓዴ ዐሻራ የዜጎችን የጋራ ተሳትፎ በማሳደግ ኃይማኖት፣ ዕድሜና ጾታ ሳይገድባቸው ኢትዮጵያውያንን በአንድ ዓላማ ያሰባሰበ ሀገራዊ የልማት አጀንዳ መሆኑን ተናግረዋል።
መርሃ ግብሩ በሀገር ጉዳይ በጋራ መሥራት ያለውን ጠቀሜታ ያሳየና ሕብረ ብሔራዊ አንድነትን ያጠናከረ መሆኑን ጠቅሰዋል።
ከኢኮኖሚ አኳያም አረንጓዴ ዐሻራ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ የገጠርና የከተማ ኢኮኖሚን ለማጠናከር እንዲሁም በቤተሰብ ደረጃ የተሻለ ኑሮ ለመፍጠር አስተዋፅኦ እያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።
የኢትጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ በበኩላቸው፤ ኢዜአ እንደ ተቋም በአረንጓዴ ዐሻራ መርሃ ግብር ያለውን ተሳትፎ አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።
በቢሾፍቱ ከተማ የተካሄደው የችግኝ ተከላም በዚህ ክረምት ኢዜአ ያካሄደው ሁለተኛው የአረንጓዴ ዐሻራ ተግባር ሲሆን፤ በቀጣይም በክልሎች የተለያዩ የችግኝ ተከላ መርሃ ግብሮችን እንደሚያካሂድ ገልጸዋል።
ኢዜአ ዜጎች በአረንጓዴ ዐሻራ ላይ የነቃ ተሳትፎ እንዲያደርጉ የማስገንዘብና የማንቃት ሥራውን በተጠናከረ መልኩ እንደሚቀጥልም አረጋግጠዋል።