በዞኑ ለመኸር እርሻ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በዞኑ ለመኸር እርሻ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ ነው
ምስራቅ ጎጃም፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፡-በምስራቅ ጎጃም ዞን ለመኸር እርሻ የሚውል ከአንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ ዘመናዊ የአፈር ማዳበሪያ እየተሰራጨ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ጥላሁን ንጋቱ ለኢዜአ እንደገለፁት፤ በዘንድሮው ዓመት የመኸር ወቅት ማዳበሪያን ጨምሮ የተለያዮ ግብአቶች ጥቅም ላይ እንዲውሉ በማድረግ ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት ታቅዶ ወደ ስራ ተገብቷል።
ለዚህም ከአንድ ነጥብ አንድ ሚሊዮን ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ ወደ ዞኑ በማስገባት የስርጭት ስራ መጀመሩን ነው የገለጹት።
ወደ ዞኑ ከገባው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥም ከ980 ሺህ ኩንታል በላይ የሚሆነው ለአርሶ አደሩ ተደራሽ የተደረገ ሲሆን ቀሪው በስርጭት ላይ እንደሆነም ነው የገለጹት።
የማዳበሪያ አቅርቦቱ ምርታማነትን በማሳደግ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለገበያ የሚተርፍ ምርት ለማምረት የራሱ የሆነ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አስገንዝበዋል።
በዞኑ የጎዛምን ወረዳ የጥጃን ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር አያሌው ክፋሌ ፤ ለምርት ማሳደጊያ የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ በወቅቱ መቅረቡ የዘር ስራችን በተገቢው መንገድ ለማከናወነ አስችሎናል ነው ያሉት።
በአሁኑ ወቅትም አራት ኩንታል የሚሆን የአፈር ማዳበሪያ በመውሰድም የበቆሎና ስንዴ ሰብል መዝራታቸውን አስረድተዋል።
የአነደድ ወረዳ የጉዳለማ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር ላመስግን መለሰ በበኩላቸው፤የአፈር ማዳበሪያ ተጠቃሚ መሆናቸው ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ እንደሚያግዛቸው ነው የተናገሩት።
የተረከቡትን ከአምስት ኩንታል በላይ የአፈር ማዳበሪያ በመጠቀም መሬታቸውን በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን እየሰሩ እንደሚገኙም አስረድተዋል።
በዞኑ በ2018/2019 የምርት ዘመን በዘር ከሚሸፈነው ማሳ ከ26 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ለማግኘት ታቅዶ እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።