በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግርን የሚያፋጥን የሰው ኃይል እየተገነባ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግርን የሚያፋጥን የሰው ኃይል እየተገነባ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ የዲጂታል ሽግግርን የሚያፋጥን የሰው ኃይል እየተገነባ መሆኑን የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) ገለጹ።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ለመጀመሪያ ጊዜ በሰው ሠራሽ አስተውሎት የሰለጠኑ ስታርት አፖችን አስመርቋል።
የኢንስቲትዩቱ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና (ዶ/ር) እንደገለጹት፤ ዲጂታል ሽግግር ጠንካራ የሰው ኃይል አቅም እንዲሁም አስተማማኝ መሠረተ ልማቶችን ይጠይቃል።
ኢንስቲትዩቱ ከተቋቋመ በአጭር ጊዜ ውስጥ ሀገሪቱን በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ተጠቃሚ የሚያደርጉ በርካታ ውጤቶች መገኘታቸውን ተናግረዋል።
በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ በአፍሪካ የመጀመሪያው የሰው ሠራሽ አስተውሎት ፖሊሲና ስትራቴጂ መቀረጹን፣ ችግር ፈቺ ውጤቶች መመረታቸውን፣ ለአለም ገበያ ብቁ የሆኑ ዲጂታል ባለሙያዎችን ማፍራት መቻሉን፣ የሰው ሠራሽ አስተውሎት መሠረተ ልማት ዝርጋታና ሌሎች ውጤቶች መገኘታቸውን ጠቅሰዋል።
በሁሉም ዘርፎች በተለይም ቅድሚያ በሚሰጣቸው የፍትህና አስተዳደር፣ ስማርት ኮርት (ዘመናዊ ፍርድ ቤት)ና ስማርት ፖሊስ ጣቢያ፣ ጤና፣ የሕዝብ አገልግሎትና በሌሎች ዘርፎች በAI የታገዙ ቴክኖሎጂዎች በስፋት ሥራ ላይ መዋላቸውን ገልጸዋል።
በዘርፉ ለተገኘው ስኬት በስታርታፕ፣ ሰመር ካምፕ፣ በትምህርት ቤቶች፣ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማትና በሌሎች ተቋማት የሰው ኃይል ልማት ጠንካራ የአቅም ግንባታ ሥራዎች በመከናወኑ ነው ብለዋል።
ለመጀመሪያ ጊዜ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የሰለጠኑት ተመራቂዎች የዲጂታል ኢኮኖሚውን ለማንቀሳቀስ ዝግጁ የሆኑ፣ የተፈተሹ፣ ሥራ ላይ የዋሉና በገበያው ሊስፋፉ የሚችሉ ውጤቶች ማቅረባቸውን ገልጸዋል።
እነዚህ ውጤቶች የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ስትራቴጂ ወደ ተግባር መሸጋገሩን እንደሚያሳዩ ተናግረዋል።
በዕለቱ በተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ሰልጣኞቹ በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በቋንቋ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ሲቲ፣ በፋይናንስ እና በሰብዓዊ ልማት ዘርፎች የሠሯቸውን ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ አቅርበዋል።