ቀጥታ፡

ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የነገውን ዓለም ታሳቢ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የሰው ኃይል እያፈራች ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ በሰው ሰራሽ አስተውሎት የነገውን ዓለም ታሳቢ በማድረግ ብሔራዊ ጥቅሟን የሚያስጠብቅ የሰው ኃይል እያፈራች መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በተገኙበት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ባለፉት ስድስት ወራት በሰው ሠራሽ አስተውሎት ያሰለጠናቸውን ስታርታፖች በይፋ አስመርቋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በምረቃ ሥነ-ሥርዓቱ ላይ እንዳሉት፤ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የነገውን ዓለም ጉዞ እየቃኘና እየወሰነ ይገኛል።

ኢትዮጵያም ይህንን ዕድል ለብሔራዊ ጥቅም ለማዋልና የነገውን ዓለም ጉዞ በብቃት ለመቃኘት ተተኪውን ትውልድ በዘርፉ የማብቃትና የማንቃት ተግባራትን እያከናወነች መሆኑን ገልጸዋል።


 

ለዚህም በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ሰልጥነው ለምረቃ የበቁት ስታርታፕ ሰልጣኞችም ትልቅ ማሳያ መሆናቸውን ተናግረዋል።

መመረቅ የመጨረሻ መዳረሻ ሳይሆን ለረጅም ጉዞ የመጀመሪያ ነው ያሉት ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በስልጠና ቆይታቸው ዕውቀትና በራስ መተማመን አቅም መገንባታቸውን ገልጸዋል።

በቀጣይም የፈጠራ ሥራዎቻቸውን በታማኝነት በማሳደግ ለሀገር የሚጠቅሙ መፍትሔዎችን እንዲያቀርቡና ኢትዮጵያን በዘርፉ ተወዳዳሪ የሚያደርጉ የቴክኖሎጂ አምባሳደሮች እንዲሆኑ አስገንዝበዋል።

መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትም የኢንስቲትዩቱን አርዓያነት ያለው ጉዞ እንዲከተሉ ጥሪ አቅርበዋል።

ኢትዮጵያ በስታርታፕ ልማት ለራሷ አልፎ ለመላው አፍሪካውያን ወጣቶች የምትተርፍ እንድትሆን ቀጣይነት ያለው ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።

በመጨረሻም ለተመራቂ ስታርታፖች መልካምና ስኬታማ የሥራ ዘመን ተመኝተዋል።

በዕለቱ በተዘጋጀው አውደ-ርዕይ ሰልጣኞቹ በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በቋንቋ ቴክኖሎጂ፣ በስማርት ሲቲ፣ በፋይናንስ እና በሰብዓዊ ልማት ዘርፎች የሠሯቸውን ችግር ፈቺ የቴክኖሎጂ ውጤቶች ለዕይታ አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም