ቀጥታ፡

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት አመት 85 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት አጸደቀ

አርባምንጭ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት አመት 85 ነጥብ 7 ቢሊየን ብር በጀት አጽድቋል።

የክልሉ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤውን በአርባምንጭ ከተማ እያካሄደ ነው።


 

የክልሉ ፕላን፣ መሠረተ ልማትና የመንግስት ሀብት አስተዳደር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ዕንቁ ዮሐንስ የክልሉ የ2019 ረቂቅ በጀት 85 ቢሊየን 774 ሚሊየን 12 ሺህ 25 ብር መሆኑን ለጉባኤው በዝርዝር አቅርበዋል።

በጀቱ ከክልሉ በሚሰበሰብ ገቢና በፌደራል መንግስት ድጋፍ የሚሸፈን መሆኑን ተናግረዋል።


 

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ሃላፊ ተፈሪ አባተ በጀቱ በክልሉ ፍትሃዊ ልማት በማረጋገጥ የህብረተሰቡን አዳጊ ፊላጎት ለመመለስ ያለመ መሆኑን አብራርተዋል።

በጀቱ በተለይም በድህነት ቀናሽ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረገ መሆኑን ገልጸዋል።

እንዲሁም ተቋማት ለስራ ምቹ እንዲሆኑ የማደራጀትና ወቅቱ የደረሰበትን የዲጂታል ቴክኖሎጂ በመጠቀም ሁለንተናዊ የልማት ትልሞችን ለማሳካት ትኩረት መደረጉንም አመልክተዋል።

በኢኮኖሚው መዋቅራዊ ሽግግር ለማምጣት የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርትና ምርታማነትን ለማላቅ፣ በሜካናይዜሽን በመታገዝ የግብርና ክፍለ ኢኮኖሚ ለማሳደግ ብሎም ለመሠረተ ልማት፣ ለትምህርት እና ለጤና ልማት አጽንኦት መሰጠቱን አስታውቀዋል።

የምክር ቤቱ አባላት በቀረበው ረቂቅ በጀት ዙሪያ ውይይት በማድረግ አጽድቀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም