ቀጥታ፡

የሀገራችንን መዳረሻ በራሳችን ዕውቀትና ጥበብ እንቀርጻለን - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ የወደፊት ዕጣ ፈንታዋንና መዳረሻዋን ሌሎችን ጣልቃ ሳታስገባ በራሷ ዕውቀት እና ጥበብ ትቀርጻለች ሲሉ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገጻቸው ባስተላለፉት መልዕክት፤ በኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት አማካኝነት በሀገሪቱ ታሪክ የመጀመሪያዎቹን የኤአይ ስታርትአፕ ሠልጣኞች በሳይንስ ሙዚየም ዛሬ በድምቀት ማስመረቃቸውን ጠቁመዋል።


 

እኛ የወደፊቱን ዕጣ ፈንታችንን እና መዳረሻችንን ሌሎች እንዲወስኑ አንጠብቅም አንፈቅድም፤ ይልቁንም በሀገራችን ጥበብ፣ በራሳችን ዕውቀት እንቀርጸዋለን ሲሉ ተናግረዋል።

ይህም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ለዘርፉ የሰጡት ልዩ ትኩረትና የቅርብ ክትትል ፍሬ፣ እንዲሁም ሀገራችን በልጆቿ ጥረት ያስመዘገበችው ትልቅ የስኬት ምዕራፍ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

ወጣት ፈጣሪዎች በጤና፣ በትምህርት፣ በትራንስፖርት፣ በስማርት ሲቲ፣ በፋይናንስና በሌሎችም ዘርፎች የተሠማሩ መሆናቸውን አብራርተዋል።

በቴክኒክና የምርት ልማት ክሂሎት፣ ትክክለኛ ችግር ፈቺ የቢዝነስ አስተሳሰብ፣ ደረጃውን የጠበቀ የኤአይ ወርክሾፕ፣ የክላውድ ዳታ ማዕከል እና ከፍተኛ የኮምፒዩቲሽናል ሪሶርስ ድጋፍ ማግኘታቸውንም ነው የገለጹት።

አንድ ስታርትአፕ ሲደገፍ የላቀ ቴክኖሎጂ እንዲሁም ለብዙዎች የሥራ ዕድል ይፈጥራል፤ መንግሥታችን ለዚህ ትኩረት ሰጥቷል። የዛሬ ተመራቂዎችም ተጨባጭ ማሳያ ናቸው ብለዋል ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም