ቀጥታ፡

በክልሉ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ

ሀዋሳ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ በሲዳማ ክልል የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ አስታወቁ።

የክልሉ ትምህርት ቢሮ የ2019 የትምህርት ዘመን የትምህርት ንቅናቄ መድረክ በሀዋሳ ከተማ እየተካሔደ ነው።

ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በመድረኩ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ በክልሉ የትምህርት ስብራትን ለመጠገንና ጥራትን ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው ብለዋል።


 

ባለፉት ጥቂት ዓመታት በዘርፉ ላጋጠሙ ችግሮች ዘላቂ መፍትሔ ለመስጠት ከቅድመ መደበኛ ጀምሮ በትምህርት ዘርፉ በቅንጅት ውጤታማ ተግባራት ሲከናወን መቆየቱን አንስተዋል።

ትምህርት ቤቶችን ለመማር ማስተማር ምቹ ለማድረግና በግብአት ለማሟላትም በርካታ ተግባራት መከናወናቸውን ጠቅሰዋል።

በዚሁ ወቅት ደረጃቸውን የጠበቁ ትምህርት ቤቶች የተገነቡ ሲሆን የመማሪያ ክፍሎች ዕድሳት መደረጉንም ነው የተናገሩት።

ይህም የተማሪዎችን የመማር ፍላጎት በመጨመር በትምህርታቸው ላይ አዎንታዊ ለውጥ እንዲታይ ጉልህ ሚና እየተጫወተ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ በትምህርት ዘርፍ የታየውን ለውጥ አጠናክሮ ለማስቀጠል እንደሚሠራ አመልክተው ባለድርሻ አካላትም ለዚሁ ስኬት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ አስገንዝበዋል።


 

የክልሉ ምክትል ርዕሰ መሥተዳድርና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ በየነ በራሳ በበኩላቸው፤ ባለፉት አምስት ዓመታት በክልሉ የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የተከናወኑ ጠንካራ ሥራዎች ፍሬ እያፈሩ ነው።

የህዝብን አቅም በመጠቀም ምቹ የመማሪያ አካባቢ ለመፍጠር፣ የትምህርት ቤቶችን ደረጃ ለማሻሻልና የመምህራንን አቅም ለመገንባት በተቀናጀ መንገድ የተሠሩ ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን ነው ያነሱት።

የክልሉ መንግሥት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተገኙበት እየተሳተፉበት ባለው መድረክ የትምህርት ቢሮ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት እየቀረበ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም