የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና በማስገኘት ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና በማስገኘት ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራ አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅናን በማስገኘት ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መሆኑን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) ገለጹ።
''ፅዱ ኢትዮጵያ፤ ለትውልድ'' በሚል መሪ ሃሳብ የሚካሄደው ሦስተኛው ዙር ሀገራዊ የከተማ አቀፍ የአካባቢ ጥበቃ ንቅናቄ በይፋ ተጀምሯል።
የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ለሊሴ ነሜ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች አህጉራዊና ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና በማስገኘት ለገጽታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋትኦ እያበረከቱ ነው።
በዚህም የአካባቢ ጥበቃ ሥራ የስነ-ምኅዳር ደኅንነትን በመጠበቅ ዜጎች ጤናማና ፅዱ ከባቢ የሚኖሩበትን አስቻይ ሁኔታ እንዲፈጠር እያደረገ እንደሚገኝም ገልጸዋል።
በሦስተኛው ዙር ሀገር አቀፍ የፅዱ ኢትዮጵያ ንቅናቄም በመጀመሪያው ወር የፕላስቲክ፣ በሁለተኛው ወር የአደገኛና ኤሌክትሮኒክስ ቆሻሻ፣ በሦስተኛው ወር የድምፅ ብክለትን የመከላከል ሥራዎች እንደሚከናወኑ አብራርተዋል።
የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባና የኢንዱስትሪ ልማት ቢሮ ኃላፊ ጃንጥራር ዓባይ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የሚከናወኑ የኮሪደርና የወንዝ ዳርቻ የመሠረተ ልማት ሥራዎች የሥነ-ምኅዳር ከባቢን ከዜጎች ጤና ጥበቃ ጋር ተስናስለው የተገነቡ ናቸው ብለዋል።
በአዲስ አበባ ከተማ የፍሳሽ ቆሻሻ ማጣሪያ ጣቢያዎችን ቁጥር ወደ 44 በማሳደግ የመዲናዋን የፍሳሽ ማጣሪያ ሽፋን ወደ 43 በመቶ ማሳደግ መቻሉን ገልጸዋል።
የከተማዋን የአረንጓዴ ሽፋን በከፍተኛ ሁኔታ ለማሳደግ በተሰራው ስራም 600 ኪሎ ሜትር የሚሸፍኑ 76 ወንዞችን ከብክለት ለመጠበቅ ከፍተኛ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል።
ፅዳትና ንጽህና የከተማ ስልጣኔ መገለጫ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ አበባ ከተማ የአካባቢ ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ሥራ አስኪያጅ እሸቱ ለማ (ዶ/ር) ሲሆኑ መላው ሕብረተሰብም በንቅናቄው ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪ አቅርበዋል።