በኦሮሚያ ክልል አገልግሎቶችን ከብልሹ አሰራር የፀዱ ማድረግ የሚያስችል ሪፎርም እየተተገበረ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በኦሮሚያ ክልል አገልግሎቶችን ከብልሹ አሰራር የፀዱ ማድረግ የሚያስችል ሪፎርም እየተተገበረ ነው
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ለሕብረተሰቡ የሚሰጡ አገልግሎቶችን ከሙስና እና ብልሹ አሰራር የፀዱ ማድረግ የሚያስችል ሪፎርም ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ ተናገሩ።
''የአገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ለሁለንተናዊ ብልጽግና'' በሚል መሪ ሀሳብ የኦሮሚያ ክልል የመንግስት አገልግሎት እና አስተዳደር ሪፎርም ትግበራ ይፋ ማድረጊያ መርሃ ግብር በቢሾፍቱ ከተማ እየተካሄደ ይገኛል።
በመድረኩ የክልሉ ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ፣ የፌዴራል ሲቪል ሰርቪስ ኮሚሽነር መኩሪያ ሀይሌ (ዶ/ር)፣ የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ኮከቤ ዲዳ፣ የመንግስት ከፍተኛ የቢሮ ኃላፊዎችና አመራሮች ተገኝተዋል።
የኦሮሚያ ክልል ምክትል ፕሬዚዳንት አወሉ አብዲ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፣ የአገልግሎት አሰጣጥን ግልጽ እና ተጠያቂነት ያለው በማድረግ የሙስና እና የብልሹ አሰራር ችግሮችን መፍታት የሚያስችል ሪፎርም እየተተገበረ ይገኛል።
ከዚህ ውስጥም በክልሉ ከቀበሌ ጀምሮ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥን የተሳለጠ ማድረግ የሚያስችል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅትም የተለያዩ አልግሎቶችን በዲጂታል ስርዓት በመደገፍ የህዝቡን እንግልት፣ ጊዜና ወጪ በመቆጠብ ቀልጣፋ አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።
በየደረጃው የሚገኘው የክልሉ አመራርና ሰራተኛም ለህዝብ የሚሰጠውን አገልግሎት የተገልጋዩን እንግልት ለመቀነስ ሰፊ ጥረት እያደረጉ እንደሚገኙም አመልክተዋል።
በመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ግልጽነት፣ ተጠያቂነትና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ እንዲኖር የማድረግ ስራ ልዩ ትኩረት እንደሰጠውም ነው የገለጹት።
በአሁኑ ወቅትም የመንግስት ሰራተኞች አቅምን የማሳደግ፣ አዎንታዊ የስራ ባህልን መገንባት እና የዜጎችን እርካታ ማረጋገጥ የሚያስችል ስራዎች ተግባራዊ እየተደረጉ መሆኑን ጠቁመዋል።
በለውጡ ዓመታት በክልሉ የተለያዩ የሪፎርም ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን አመልክተው በአዲሱ በጀት ዓመትም የመንግስት አገልግሎትና አስተዳደር ሪፎርም በተሟላ መልኩ የሚተገበር ይሆናል ብለዋል።
የክልሉ የፐብሊክ ሰርቪስና የሰው ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ኮከቤ ዲዳ በበኩላቸው፣ የመንግሥት መስሪያ ቤቶችን አሰራር የማዘመንና የሰው ኃይሉን አቅም መገንባት የሚያስችል አሰራር እየተዘረጋ መሆኑን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም የአገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታል መንገድ የማደራጀት ስራ እየተሰራ ሲሆን ከዚህ ውስጥም 58 የመሶብ አንድ ማዕከል መስጫ ተቋማት አገልግሎት መጀመራቸውን ጠቅሰዋል።