በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት ተሰጥቷል
አሶሳ፤ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋት የአገልግሎት አሰጣጥን ለማዘመን ትኩረት መስጠቱን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ተናገሩ።
የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክርቤት 6ኛ ዙር 5 ዓመት 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤ እየተካሄደ ነው።
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን በጉባኤው የክልሉን የ2018 በጀት ዓመት እቅድ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በወቅቱ እንዳስታወቁት የሲቪል ሰርቪስ አገልግሎት ዘመናዊነትን የተላበሰ እና ከህዝብ ቅሬታ የፀዳ ለማድረግ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
በክልሉ የቤጉ መሶብ እና የአሶሳ መሶብ አንድ ማዕከላት አገልግሎት ከብልሹ አሰራር የፀዳ አገልግሎት እየሰጡ መሆናቸውን ገልፀው፤ ማዕከላቱ ከ16 ተቋማት የተለዩ 83 አገልግሎቶችን ተደራሽ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል።
በማዕከላቱ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ39ሺህ በላይ ዜጎች የአገልግሎት ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቁመው በዚህም የላቀ የተገልጋዮች እርካታ ደረጃ ተመዝግቧል ብልዋል።
በክልሉ የመሶብ አገልግሎትን ለማስፋፋት በተያዘው ዕቅድ መሠረት በባምባሲ፣ ከማሺ እና ግልገል በለስ ከተሞች የተገነቡ ማዕከላት በዚህ ወር መጨረሻ ወደ ስራ እንደሚገቡ አስታውቀዋል።
የክልሉ መንግስት በአገልግሎት አሰጣጥና በመልካም አስተዳደር ላይ የሚነሱ የህዝብ ቅሬታዎችን ለመፍታት በተቋማት ደረጃ የሲቪል ሰርቪስ ሪፎርም እያከናወነ መሆኑንም አንስተዋል።