ቀጥታ፡

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶች የክልሉን የመልማት አቅም ያረጋገጡ ናቸው - ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን

አሶሳ፤ ሐምሌ 18/2018 (ኢዜአ)፡- በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በክልሉ የተመዘገቡ ስኬቶች የክልሉን የመልማት አቅም ያረጋገጡ መሆናቸውን የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን ገለጹ።

የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5 ዓመት 3ኛ የሥራ ዘመን 5ኛ መደበኛ ጉባኤውን ማካሄድ ጀምሯል።

የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አሻድሊ ሀሰን የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ በበጀት ዓመቱ ክልሉ በሁሉም ዘርፎች የተከናወኑ የልማት እና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማ ናቸው።




በዋናነት የክልሉ የኢኮኖሚ ምሰሶ የሆነውን የግብርናውን ዘርፍ በማዘመን ምርትና ምርታማነትን ለማሳደግ የተከናወኑ ተግባራት በቤተሰብ ደረጃ የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ያረጋገጠ ሲሆን የኢኮኖሚ አቅሙንም ማሳደግ አስችሏል ብለዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመትም ከ55 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት መገኘቱን አመልክተው የመካናይዜሽን እርሻ ተግባራዊ በመደረጉ ምርታማነትን ማሳደግ መቻሉን ጠቅሰዋል።

በዚህም በሄክታር እስከ 34 ኩንታል ምርት ማግኝት ተችሏል ነው ያሉት በሪፖርታቸው።

በተጨማሪም ባለፉት ጥቂት ዓመታት መንግስት ለማዕድን ዘርፉ ትኩረት መስጠቱ ለክልሉ ተጨማሪ የኢኮኖሚ ምንጭ ከመሆኑ ባለፈ ለሥራ ዕድል ፈጠራ ሰፊ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ገልጸዋል።

ለአብነትም በበጀት ዓመቱ ዘርፉ ህጋዊ በሆነ መንገድ እንዲመራ በማድረግና አነስተኛ የማዕድን አምራቾችን ወደ ስራ በማስገባት ከ8 ሺህ 900 ኪሎግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ማቅረብ መቻሉን አስታውቀዋል።

በክልሉ ያለውን የልማት ፍላጎት በራስ አቅም ለመሸፈን ለማድረግም የገቢ አሰባሰብ ሂደቱን በማዘመን የተሻለ ገቢ መሰብሰብ መቻሉን አመላክተዋል።

በአጠቃላይ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተመዘገቡ ስኬቶች የክልሉን የመልማት አቅም ያረጋገጡና የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ያሳደጉ መሆናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም