ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ለውጥ መዲናዋን ከአህጉራዊ የቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ የአፍሪካ የቱሪዝም ማዕከልነት አሳድጓታል - ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 18/2018(ኢዜአ)፦ የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ለውጥ መዲናዋን ከአህጉራዊ የቱሪስቶች መሸጋገሪያነት ወደ የአፍሪካ የቱሪዝም ማዕከልነት ማሳደጉን የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ገለጹ።

ፐልስ ኦፍ አፍሪካ የሚዲያ ተቋም (POA) እና የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን በቱሪዝም ዘርፍ በቅርበት መስራት የሚያስችል የትብብር ስምምነት ተፈራርመዋል።

ስምምነቱን የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ እና የአዲስ አበባ ቱሪዝም ኮሚሽን ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ ፈርመውታል።

ኮሚሽነር ሁንዴ ከበደ በፊርማ ሥነ-ሥርዓቱ እንደገለጹት፤ ስምምነቱ ቀደም ሲል በነበረው የትብብር የሥራ ግንኙነት ላይ የላቀ እሴት በመጨመር ወደ ከፍተኛ የአጋርነት ደረጃ የሚያሸጋግር ነው።


 

ስምምነቱ የአዲስ አበባን ሁለንተናዊ የቱሪዝም እመርታ በሰፊው በማስተዋወቅ የቱሪዝም እንቅስቃሴን ለማጠናከርና የዘርፉን ዕድገት ለማፋጠን ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

አዲስ አበባ በቅርብ ዓመታት በርካታ የቱሪዝም መዳረሻዎችና ዘመናዊ መሠረተ ልማቶች የተገነቡባት አፍሪካዊት የከተሜነት አብነት እየሆነች እንደሚገኝም ተናግረዋል።

ለአብነትም በኮንፍረንስ ቱሪዝም አዲስ አበባ የአህጉሪቱ ቀዳሚ ማዕከል መሆኗን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 221 ዓለም አቀፍ ጉባኤዎችን በስኬት ማስተናገድ እንደተቻለ አስረድተዋል።

የአዲስ አበባ ሁለንተናዊ ለውጥ መዲናዋን ከአህጉራዊ የቱሪስት መሸጋገሪያነት ወደ የአፍሪካ የቱሪዝም ማዕከልነት እንዳሳደጋት ማሳያ መሆኑን አንስተዋል።

የአዲስ አበባን የልማትና የቱሪዝም እመርታዎች በሰፊው ለማስተዋወቅ፣ ገጽታ ለመገንባትና የቱሪዝም ፍሰትን ለማሳደግ ሰፊ ልምድ ካላቸው የሚዲያ ተቋማት ጋር መተባበር ወሳኝ ነው ብለዋል።


 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈፃሚ ሰይፈ ደርቤ እንደተናገሩት፤ ኢዜአ ብሔራዊ ጥቅምን በማስቀደም፣ የሀገር ገጽታን በመገንባትና የሕዝቦችን አብሮነት በማጠናከር በኩል በትኩረት እየሠራ ነው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት በታሪክ ውስጥ የአፍሪካ ሕዝቦች ከቅኝ ግዛት ነፃ እንዲወጡ በመረጃና በዜና ድጋፍ ገንቢ ሚና የተጫወተ አንጋፋ ተቋም መሆኑንም አስታውሰዋል።

በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዕሳቤ መሠረት የቅድመ አያቶችን የፓን አፍሪካኒዝም ርዕይ ለማስቀጠል አፍሪካውያን የራሳቸውን ታሪክ በራሳቸው ድምጽ የሚናገሩበት ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) የሚዲያ ተቋም ወደ ሥራ መግባቱን አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅትም ፐልስ ኦፍ አፍሪካ (POA) የሚዲያ ተቋም የአፍሪካን የተዛቡ ትርክቶች በማረምና አህጉሪቱን በተጨባጭ እውነታዎች በማቅረብ የተሻለ ዓለም አቀፍ ገጽታ ለመገንባት እየሠራ ነው ብለዋል።

በዚህም የአዲስ አበባን የቱሪዝም ፀጋዎችና የልማት እመርታዎች ለሀገር ውስጥና ለውጭ ታዳሚዎች በሰፊው በማስተዋወቅ ከፍተኛ ሚና እንደሚወጣ ተናግረዋል።

የትብብር ስምምነቱም የመዲናዋን ገጽታ ከማስተዋወቅ ባሻገር አፍሪካውያን የአዲስ አበባን የልማት ሥራዎች እንዲያውቁ በማስቻል የቱሪዝም ፍሰትን ለማሳደግ ጉልህ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ገልጸዋል።

በቀጣይም የትብብር ስምምነቱን ወደ ተጨባጭ ውጤት በመቀየር በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ቋንቋዎች በትኩረት በመስራት የአዲስ አበባን የቱሪዝም አቅም ለዓለም ለማስተዋወቅ እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም