የኮሪደር ልማት ትሩፋቶች፤ የከተሞች ህዳሴ - ኢዜአ አማርኛ
የኮሪደር ልማት ትሩፋቶች፤ የከተሞች ህዳሴ
በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች የተጀመረው ሰፊ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የመንገድ ጥገና ወይም የማስዋብ ስራ ብቻ ሳይሆን፤ የከተሞች አወቃቀር፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የማህበራዊ ህይወት ገጽታ ሙሉ በሙሉ የለወጠ ሥር ነቀል ከተማን የማደስ ትልቅ ስራ ነው።
የከተማ እና መሰረተ ልማት ሚኒስቴር ይፋ ባደረገው መረጃ መሠረት፣ በአሁኑ ወቅት የኮሪደር ልማቱ በአዲስ አበባ ከተገኘው ስኬት በመነሳት ወደ 75 በሚጠጉ የሀገሪቱ ዋና ዋና ከተሞችና ታዳጊ ከተሞች ተስፋፍቷል። ይህም ሀገሪቱ ከተበታተነና ጥራት ከጎደለው የመሰረተ ልማት አሰራር ወጥታ ወደ ዘመናዊና የተቀናጀ የከተሜነት ምዕራፍ መሸጋገሯን ያመላክታል።
የኮሪደር ልማቱ ከዚህ ቀደም የነበሩ የከተሞች መዋቅራዊ ችግሮችን በጥቅሉ የፈታ ሲሆን፤ ዋና ዋናዎቹ የለውጥ መስኮች በሚከተሉት ነጥቦች ይጠቃለላሉ።
አካታች የመንገድና የትራፊክ ፍሰት
ቀደም ሲል መንገዶች ለባለሞተር ተሽከርካሪዎች ብቻ ያደሉ በመሆናቸው ለትራፊክ መጨናነቅና ለሚከሰቱ አደጋዎች ምክንያት ሆነው ቆይተዋል። የኮሪደር ልማቱ ሰፊ የእግረኛ፣ የብስክሌትና የስፖርት ማሳለጫ መንገዶችን፣ አየር ላይና ከመሬት በታች ድልድዮችን እንዲሁም ዘመናዊ የታክሲና አውቶቡስ ማቆሚያዎችን አካቶ ተገንብቷል።
የተቀናጀ የመሬት ውስጥ የመሰረተ ልማት ዝርጋታ
ተደጋጋሚ የመንገድ ቁፋሮዎችንና ብክነትን ለማስቀረት የውሃ፣ የኤሌትሪክ ኃይል፣ የቴሌኮም እና የፍሳሽ መስመሮች በመሬት ሥር እንዲያልፉ ተደርጓል። ይህም ከተሞችን በአየር ከተንጠለጠሉ ገመዶች ነፃ እያደረገ ይገኛል። በተጨማሪም በክረምት ወቅት የሚከሰተውን የጎርፍ አደጋ በከፍተኛ ደረጃ መቀነስ እያስቻሉም ይገኛሉ።
የ24 ሰዓት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴና አረንጓዴ ሥፍራዎች፦
በኮሪደር ልማቱ ባዶና ቆሻሻ መጣያ የነበሩ ስፍራዎች ወደ አረንጓዴ መናፈሻዎችና የሕዝብ መዝናኛዎች ተቀይረዋል። ዘመናዊ የመንገድና የህንጻ መብራቶች መገጠማቸው ደግሞ የደህንነት ስሜትን በመጨመር የሌሊት የንግድ እንቅስቃሴ እንዲነቃቃ አድርጓል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሪደር ልማትን በተመለከተ ምን አሉ?
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) እንደደገለጹት፣ የኮሪደር ልማቱ የመንገድ ግንባታ ብቻ ሳይሆን የሀገሪቱን የከተሞች ደረጃ የሚያሻሽልና የዜጎችን ሥነ-ልቦና የሚያንጽ ስትራቴጂያዊ ፕሮጀክት ነው። ኢትዮጵያ በታሪኳ ትልቅ ሀገር ነች፤ ስለዚህ ከተሞቻችንም ያንን ታላቅነታችንን የሚመጥን ፅዱ፣ አረንጓዴ እና ዘመናዊ ገጽታ ሊኖራቸው ይገባል ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የሀገር ግንባታ ቀጣይነት ያለው ሂደት መሆኑን በመግለጽ፣ ይህ ልማት ድህነትንና ቆሻሻን አለመቀበልን የሚያሳይ፣ ለቀጣይ ትውልድ የሚተላለፍ ኢትዮጵያን የመስራት ጉዞ አካል መሆኑንም ጠቁመዋል። በተጨማሪም በአዲስ አበባ የተገኘው ተሞክሮ ወደ አርባ ምንጭ፣ ባህር ዳር፣ አዳማ፣ ሀዋሳ እና ድሬዳዋ በመስፋፋቱ ፕሮጀክቱ በመላ ሀገሪቱ የሥራ ዕድል በመፍጠር በኩል ከፍተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል።
ምሁራን በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማት የከተሞችን ገጽታ ሙሉ በሙሉ በመቀየር አዲስ ምዕራፍ የከፈተ መሆኑን ያነሳሉ።
የከተማ ፕላንና ዲዛይን ባለሙያ ኢንጂነር አበበ ደሴ እንደሚሉት፤ የኮሪደር ልማቱ ለብዙ ዓመታት ሳይቀናጁ የዘለቁ እንደ የውሃ፣ የኤሌክትሪክ ሃይል፣ የቴሌኮም እና የፍሳሽ መስመሮች የመሳሰሉ የመሰረተ ልማት አውታሮችን በአንድ ላይ አቀናጅቶ በመሬት ሥር እንዲያልፉ ማድረጉ የከተሞችን እድሜ የሚያራዝምና አላስፈላጊ ተደጋጋሚ ቁፋሮዎችን ያስቀረ ትልቅ ሙያዊ እርምጃ ነው።
የከተማ ልማትና አስተዳደር ምሁር በላይ አሰፋ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማቱ የከተሞችን የቦታ አጠቃቀም ቅልጥፍና ያሻሻለ መሆኑን ይገልጻሉ። ቀደም ሲል ለቆሻሻ መጣያነትና ለሕገ-ወጥ ሥራዎች ይውሉ የነበሩ ቦታዎች ወደ ሕዝብ መናፈሻነትና አረንጓዴ ሥፍራነት መቀየራቸው የከተሞችን የሥነ-ምህዳር ሚዛን ለመጠበቅ እንደሚረዳ ነው የተናገሩት።
የኢኮኖሚ ምሁሩ ቆስጠንጢኖስ በርኸ ተስፋ(ዶ/ር)፤ የኮሪደር ልማት በምሽት ጭምር ንግድ ማካሄድ የሚቻልበት አውድ የፈጠረ መሆኑን ይጠቅሳሉ። የከተሞች የኢኮኖሚ እንቅስቃሴን በማሳለጥ በኩል ዓይነተኛ ሚና እየተጫወተ ይገኛል ነው ያሉት።
ማጠቃለያ
በአጠቃላይ፣ የኮሪደር ልማት ፕሮጀክት የኢትዮጵያን ከተሞች ከነበሩበት የተጨናነቀና ኋላቀር ገጽታ አውጥቶ ወደ ዘመናዊ፣ ፅዱ እና ለኢንቨስትመንት ሳቢ ወደሆኑ የከተማ ማዕከላት የመቀየር ትልቅ አዎንታዊ አስተዋጽኦ አበርክቷል። ይህም የኢትዮጵያን ገጽታ በመቀየር በአፍሪካም ተጠቃሽ ሀገር እያደረጋት ይገኛል፤ ከሥራ ዕድል ፈጠራ አኳያም የኮሪደር ልማት ሰፊ አስተዋጽኦ እያበረከተ ከመሆኑም ባለፈ ፕሮክቶችን በአጭር ጊዜ ጀምሮ የመጨረስ ማሳያ ተደርጎም ይወሰዳል።