ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ለተከታታይ ዓመታት በውጤታማነት እንዲቀጥል አስችሎታል - ኢዜአ አማርኛ
ኮርፖሬሽኑ ያደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ለተከታታይ ዓመታት በውጤታማነት እንዲቀጥል አስችሎታል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፦ ሁለንተናዊ ሀገራዊ ለውጡን መነሻ ያደረገው ተቋማዊ ሪፎርም ለተከታታይ ዓመታት ውጤታማነቱ እንዲረጋገጥ እንዳስቻለው የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ገለፀ።
የኮርፖሬሽኑ በ2019 በጀት ዓመትም ይህንኑ አጠናክሮ ለማስቀጠል የሚያስችል ስትራቴጂካዊ አቅጣጫም ተቀምጧል።
ኮርፖሬሽኑ የ2018 በጀት ዓመት የሥራ አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ውይይቱን አካሂዷል።
በዚህ የግምገማ መድረክ በበጀት ዓመቱ የተቀመጠውን ዕቅድ 97 በመቶ ማከናወን መቻሉ የተገለፀ ሲሆን፣ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በገቢ ዕድገት፣ በቤት ልማት፣ በመስፈጸም አቅም እና በቤት አስተዳደር ረገድ የተከናወኑት ሥራዎች የተቋሙን አጠቃላይ የለውጥ ጉዞ ማረጋገጣቸው ተጠቁሟል።
በተጨማሪም የሕዝብና የመንግስት ጥቅም ለማስጠበቅ በፍርድ ቤት በተከናወኑ ክርክሮች በርካታ ይዞታዎችን ማስመለስ ተችሏል ብሏል።
ኮርፖሬሽኑ በምሥራቅ አፍሪካ እና በአፍሪካ ገበያ ለመሰማራት ያስቀመጠውን ራዕይ ለማሳካት በሚያደርገው ጥረት፣ በደቡብ ሱዳን ጁባ ከተማ በቤት ልማት ለመሳተፍ ከደቡብ ሱዳን ኢኳቶሪያል ስቴት ጋር የተደረሰው ስምምነት ወደ ተግባር ለማስገባት ሥራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ አስታውቋል።
የልማት ፕሮጀክቶችን በተመለከተ የፒያሳ እና የጎልድ ሳይት ፕሮጀክቶችን አጠናቆ ወደ አገልግሎት ማስገባት የተቻለ ሲሆን፣ ዘመናዊ የ3ዲ የግንባታ ቴክኖሎጂን ለማስፋፋት የሚያስችሉ የመጀመሪያዎቹ የሙከራ ቤቶች ግንባታም በመከናወን ላይ ይገኛሉ።
በሌላ በኩል የቤቶች ቆጠራና የመረጃ ማሰባሰብ ሥራ በመጠናቀቁ ዘመናዊ የቤት አስተዳደር ሥርዓትን ማጠናከር የተቻለ ሲሆን፣ በርካታ የንግድ ቤቶችም ከደንበኞች ጋር በትብብር ተገንብተው ወደ ኪራይ አገልግሎት በመግባታቸው ከፍተኛ ገቢ ማስገኘት ጀምረዋል።
ከዚህ ባሻገር የተቋሙን የ50 ዓመት የጉዞ ታሪክና ስኬቶች የሚያስተዋውቁ የተለያዩ መርሐግብሮች በኢዮቤልዩ በዓሉ ወቅት ለአራት ተከታታይ ቀናት በታላቅ ድምቀት ተከብረዋል። በዚህም የተቋሙን ገጽታ መቀየር መቻሉም ነው የተገለጸው፡፡
በአዲሱ የ2019 በጀት ዓመት ዘመናዊና ፈጣን የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በስፋት ሥራ ላይ ማዋል፣ የሀገር ውስጥ የቤት አቅርቦትን ለማሳደግ ሰፋፊ የቤት ልማት መርሐግብሮችን መተግበር፣ አዳዲስ አሰራሮችን በመጠቀም የገቢ ምንጮችንና የፋይናንስ አማራጮችን ማስፋፋት እንዲሁም የሰው ኃይል እና የአሰራር ሥርዓት አቅምን ማጠናከር ዋነኛ ስትራቴጂካዊ የትኩረት አቅጣጫዎች ሆነው ተቀምጠዋል።
ኮርፖሬሽኑ በአዲሱ የበጀት ዓመት የግንባታ ቴክኖሎጂዎችን በማስፋፋት ለአገራዊ የቤት ልማት ዕቅድ ስኬት በቁርጠኝነት እንደሚሰራ አስታውቋል።