ቀጥታ፡

በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ አዲስ የመግባባትና የአንድነት ታሪክ እየተጻፈ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ አዲስ የመግባባትና የአንድነት ታሪክ እየተጻፈ መሆኑን ዑስታዝ ጀማል በሽር ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ለምክክር የቀረቡ ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በእነዚህ አጀንዳዎች ላይም 4ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ከሐምሌ 13 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተመካከሩ ይገኛሉ።

ዑስታዝ ጀማል ለኢዜአ በሰጡት አስተያየትም፤ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤው በኢትዮጵያ አዲስ ታሪክ እየተጻፈበት መሆኑን ጠቁመዋል።

ከዚህ ቀደም በነበሩ ሥርዓቶች ውሳኔዎች ከላይ ወደ ሕዝብ የሚወርዱበት አሰራር እንደነበር አስታውሰው፤ አሁን ግን ሕዝቦች በመመካከር በጋራ ውሳኔ የሚደርሱበት አውድ ተፈጥሯል ብለዋል።

የምክክር ጉባኤም ''ኢትዮጵያ እየመከረች ነው'' የሚለውን መሪ ሃሳብ በሚመጥን መልኩ በሕዝብ ወኪል በሆኑ ተመናካካሪዎች መካከል ግልፅና አሳታፊ ምክክር እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።

ከሂደቱም የሚጠበቁ ምክረ ሀሳቦች ለኢትዮጵያና ሕዝቦቿ ዘላቂ ሰላም፣ መረጋጋትና ዕድገት የሚያግዙ ውጤቶችን የሚያመጣ መሆኑን ተናግረዋል።

በዓለም ላይ በምክክር ችግሮቻቸውን የፈቱ ሀገራት ብዙ ናቸው ያሉት ተመካካሪው፤ የምክክር ጉባኤውም በኢትዮጵያውያን ግልጽ ተሳትፎ መመራቱ ሀገራዊ መግባባትን መፍጠር እንደሚያስችል እንደሆነ አስረድተዋል።

ከምክክሩ የሚወጡ ምክረ ሀሳቦች በባለድርሻ አካላት ተግባራዊ ሆነው የሕዝቦችን ተጠቃሚነትና የሀገርን የጋራ ጥቅም የሚያሳድጉ ውጤቶች እንደሚያመጡ ያላቸውን እምነት ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሀሳቦችን ወደ አንድ የጋራ መግባባት ለማምጣት የተከፈተ ታላቅ መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።

በምክክር የሚገነባው መግባባትም ለኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላምና የጋራ ብልፅግና መሰረት እንደሚሆን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም