የድሬዳዋ አስተዳደር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የድሬዳዋ አስተዳደር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ ነው
ድሬደዋ፣ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦የድሬዳዋ አስተዳደር ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስርን የሚያጠናክሩ ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን አስታወቀ።
ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህን ጨምሮ የድሬዳዋ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች ለቅዱስ ገብርኤል አመታዊ ንግስ በአል ድሬዳዋ ለመጡ ምዕመናንና እንግዶች አቀባበል አድርገዋል።
የድሬዳዋ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ሀርቢ ቡህ በወቅቱ እንዳሉት፥ ከተማዋ በህብረ ብሔራዊ አንድነት የደመቀች በመሆኗ የዜጎችን ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ለሚያጠናክሩ ተግባራት ትኩረት በመስጠት እየተከናወኑ ነው።
ድሬዳዋ እንግዶችን በፍቅር የመቀበል ልምድ ያላት መሆኗም የዚሁ መገለጫ መሆኑን ጠቁመው የዛሬው አቀባበልም ይህንኑ በተግባር ያረጋገጠ መሆኑን ተናግረዋል።
ከተማዋ የሰላም፣ የልማትና የፍቅር ተምሳሌት በመሆኗም ለኃይማኖታዊም ሆነ ሌሎች ሁነቶች ተመራጭነቷ እያደገ መምጣቱን አመልክተዋል።
ድሬዳዋ የዜጎች የርስ በርስ ትስስር ለማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ግንኙነት መጠናከር መሰረት መሆኑን በተግባር አሳይታለች ያሉት ደግሞ በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የመንግስት ዋና ተጠሪ አቶ ኢብራሂም ዩሱፍ ናቸው።
የድሬዳዋ አስተዳደር ፖሊስ ጠቅላይ መምሪያ ዋና አዛዥ ኮሚሽነር አለሙ መግራ በበኩላቸው መምሪያው የቁሉቢ ገብርኤል አመታዊ ንግስ በአል ታዳሚዎች በድሬዳዋ ቆይታቸው ሰላማዊ ጊዜ እንዲያሳልፉ ዝግጅት መደረጉን ተናግረዋል።
ለኃይማኖታዊ ክብረ በአሉ ወደ ድሬዳዋ ከመጡ ምዕመናን መካከል አቶ ስዩም ታደሰ እና አቶ የፈቃዱ አስናቀ ለኢዜአ እንዳሉት፤ የአስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮችና ነዋሪዎች ያደረጉላቸው አቀባበልና መስተንግዶ አስደስቷቸዋል።