ቀጥታ፡

በሀረሪ ክልል በበጀት ዓመቱ 6 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዷል

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ የሀረሪ ክልል ገቢዎች ቢሮ በተያዘው በጀት ዓመት 6 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ተግባር መገባቱን አስታወቀ።

በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት መሰጠቱም ተመላክቷል።

የቢሮ ኃላፊው ያሲን አብዱላሂ እንደገለጹት በ2019 በጀት ዓመት የግብር ዘመን 6 ነጥብ 4 ቢሊየን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ከሐምሌ 1/2018 ጀምሮ ሥራው መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡

ባለፉት ሁለት ዓመታት የገቢ አሰባሰብ ሥራው በቴክኖሎጂ መታገዙ፣ የባለሙያዎች አቅም መገንባቱና የገቢ ምንጮችን ማስፋት በመቻሉ ገቢን ማሳደግ ተችሏልም ነው ያሉት፡፡

በተያዘው የግብር ዘመንም የተጨማሪ እሴት ታክስ ገቢን የማሳደግ፣ ከቅጥር የሚገኝ ገቢን እና የአከራይ ተከራይ ገቢን አሟጦ የመሰብሰብ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል፡፡

በክልሉ ካለፉት ሁለት ዓመታት ጀምሮ ከጥሬ ገንዘብ ንክኪ ነፃ የሆነ የገቢ አሰባሰብ ሥርዐት በመዘርጋት በባንክ የክፍያ ማረጋገጫ ብቻ ገቢ እየተሰበሰበ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡

በክልሉ ኢኮኖሚው የሚያመነጨውን ገቢ አሟጦ በመሰብሰብ የነዋሪዎችን የመሠረተ ልማትና የአገልግሎት አቅርቦት ጥያቄዎች ለመመለስ ትኩረት መሰጠቱንም አመልክተዋል።

ከሐምሌ 1 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ እየተካሄደ ባለው የገቢ አሰባሰብ ሂደት ግብር ከፋዮች ግብራቸውን እየከፈሉ እንደሚገኙም አቶ ያሲን ጠቁመዋል፡፡

ደንበኛ ተኮር አገልግሎት እየተሰጠ መሆኑን ጠቁመው ሊፈጠር የሚችለውን ጫና ለመቀነስና ለግብር ከፋዩ አማራጭ የአገልግሎት ጊዜ ለመስጠት ሲባልም በዚህ የግብር ወቅት በተወሰኑ ሠራተኞች እስከ ምሽቱ 2 ሰአት ድረስ አገልግሎት የሚሠጥ መሆኑን ገልፀዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም