ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ጠንካራ ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ዕድል የሚፈጥር ነው - ተመካካሪዎች

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ጉባኤ ብሔራዊ መግባባትን በመፍጠር ጠንካራ ሀገርን ለመጪው ትውልድ ለማስረከብ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን ተመካካሪ ወጣቶች ገለጹ፡፡

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ካሉ ኢትዮጵያውያን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት አጀንዳዎችን ይፋ ማድረጉ ይታወሳል።

በአጀንዳዎቹ ላይም አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል ውይይት ማድረግ ጀምረዋል።

በሀገራዊ ምክክሩ እየተሳተፉ የሚገኙ ወጣቶች ለኢዜአ እንዳሉት፣ የምክክር መድረኩ በኢትዮጵያ የቆዩ ችግሮችን በምክክር በመፍታት ጠንካራ ሀገረ መንግስት ለመገንባት ትልቅ መሰረት የሚጥል ነው።


 

ከአስተያየት ሰጪዎች መካከል ወጣት ማርቆስ ገዛኸኝ፤ ከተለያዩ አካባቢዎች ከመጡ ኢትዮጵያውያን ጋር በሀገር ጉዳይ ለመመካከር ዕድል በማግኘቱ መደሰቱን ገልጿል።

ሀገራዊ ምክክሩ አንድነትና አብሮነትን በማጎልበት ጠንካራ ሀገረ መንግስት መገንባት እንደሚያስችል ገልጾ፤ ይህም የሀገሪቱን ዘላቂ ዕድገትና ብልፅግና እንደሚያፋጥን ተናግሯል።


 

ሌላኛዋ አስተያየት ሰጪ ወጣት ማርታ ተሰማ በበኩሏ፣ በሀገራዊ ምክክሩ ሁሉም ተሳታፊዎች ይበጃል ያሉትን ሃሳብ በነጻነት የሚያንጸባርቁበት መድረክ መፈጠሩን ገልጻለች።

ከምክክሩ በኋላም ጠንካራና በሁለንተናዊ መልኩ የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት መጓጓቷን ተናግራለች። 


 

ሀገራዊ ምክክሩ ወጣቶች የምክክር ባህል እንዲያዳብሩና ለሀገር ዘላቂ ሰላምና መግባባት ጠቃሚ ሀሳቦችን እንዲያበረክቱ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን የተናገረው ደግሞ ወጣት ሮብላሂ አህመድ ነው።

ወጣቶች በምክክሩ መሳተፋቸው ከአባቶች ልምድና እውቀት ከመቅስም ባሻገር ለሀገሩ መጻኢ ተስፋ የራሳቸውን አሻራ እንዲያኖሩ የሚያስችል ነው ብሏል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም