ቀጥታ፡

በክልሉ እየተከናወነ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተቸገሩ ወገኖች አለኝታና የመረዳዳት እሴት እንዲጠናከር እያደረገ ነው

ሆሳዕና፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል እየተከናወነ ያለው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተቸገሩ ወገኖች አለኝታ ከመሆን ባለፈ የመረዳዳት እሴት እንዲጠናከር እያደረገ መሆኑን የክልሉ የመንግሥት ዋና ተጠሪ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን በሆሳዕና ከተማ ለስድስት አቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤት ግንባታና ለ1 ሺህ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ አስጀምሯል።


 

በመርሐ ግብሩ የተገኙት ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) እንዳሉት በክልሉ የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ለተቸገሩ ወገኖች አለኝታ ከመሆን ባለፈ የመረዳዳት እሴት እንዲጠናከር እያደረገ ይገኛል።

በተያዘው ክረምትም አገልግሎቱን በማስቀጠል በርካታ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ ከማድረግ ባለፈ የመንግሥት ወጪ እንዲቀንስ አስችሏል ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ አገልግሎቱን ለማሳካት ከአጋር አካላት ጋር ሲሠራ መቆየቱን አንስተው፣ በሆሳዕና ከተማ ለአቅመ ደካሞች ቤት ለመገንባት የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ያስጀመረው ሥራም የተጀመረው ጥረት አካል መሆኑን ገልጸዋል።


 

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አዱኛ ደበላ (ዶ/ር) ባለሥልጣኑ በክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በሆሳዕና ከተማ ለስድስት አቅመ ደካሞች የመኖሪያ ቤቶችን የመገንባትና ለ1 ሺህ ተማሪዎች የመማሪያ ቁሳቁስ ድጋፍ የማሰባሰብ ሥራ መጀመሩን ጠቅሰዋል።


 

የሆሳዕና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ሳሙኤል ሽጉጤ በበኩላቸው፣ በከተማው በ16 የተለያዩ ዘርፎች ከ2 ሺህ በላይ ነዋሪዎችን ተጠቃሚ የሚያደርግ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት እየተሰጠ ይገኛል።

የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን ሠራተኞች በከተማው በአገልግሎቱ ለመሳተፍ ያሳዩት ቁርጠኝነት በከተማው የተጀመረውን የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራ ለማጠናከር አጋዥ ስለመሆኑም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም