ቀጥታ፡

ሀገራዊ ምክክሩ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ወደ አንድነት የሚመጡበትን የስምምነት ውል በመፈጸም ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ትልቅ አምድ ነው

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ ሀገራዊ ምክክሩ ዜጎች በሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ወደ አንድነት የሚመጡበትን የስምምነት ውል በመፈጸም ጠንካራ ኢትዮጵያን መገንባት የሚያስችል ትልቅ አምድ መሆኑን የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ገለጹ።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያውያንን በማሳተፍ ምክክር የሚደረግባቸውን ስምንት አጀንዳዎች በመለየት ከሀምሌ 8 ቀን 2018 ዓም ጀምሮ አራት ሺህ ተመካካሪዎች በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬሽን ማዕከል ዋናውን ምክክር እያካሄዱ ይገኛሉ፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (/) በተገኙበት የተጀመረው ታሪካዊው የሀገራዊ ምክክር ሂደት በኢትዮጵያውያን መካከል ግልጽ ውይይት በማድረግ ሀገራዊ መግባባትና ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን መሰረት የሚጥል ነው፡፡


 

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ምክትል አፈ ጉባኤ ዛህራ ሁመድ ለኢዜአ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የአለመግባባት ምንጮች በሰለጠነ የሀሳብ ትግል ለመፍታት ምክክር እየተደረገ ነው፡፡

በኢትዮጵየ ለዘመናት እየተንከባለሉ የመጡ አለመግባባቶች የጋራ ችግሮች በመሆናቸው የችግሮች መፍትሔም የጋራ ድል መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ኢትዮጵያ የብዝሃ ባህልና ማንነት ህዝቦች መገኛ መሆኗን ገልጸው፤ ታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር በህዝቦች መካከል ዘላቂ አብሮነት አንድነትና እኩልነትን ማርጋገጥ ያስችላል ብለዋል፡፡

ሀገራዊ ምክክሩ የበለጸገችና ያደገች ኢትዮጵያን ለቀጣዩ ትልውድ ለማሸጋገር  መሰረት የሚጥሉ ወሳኝ ሀሳቦች የሚመነጩበት መድረክ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ምክክሩ ጠንካራ ሀገረ መንግስት በመመስረት ለባዳና ባንዳ የማትመች ኢትዮጵያን እውን ማድረግ የሚያስችል ወሳኝ የታሪክ ምዕራፍ መሆኑንም አንስተዋል፡፡

የፌደሬሽን ምክር ቤት ለምክክሩ ስኬት ከኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ምስረታ ጀምሮ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን በመግለጽ፤ ሁሉም የድርሻውን መወጣት አለበት ብለዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም