የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀማችን ወጪን ከመቀነስ ባለፈ ምርታማነታችን እያሳደገልን ነው - አርሶ አደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የተፈጥሮ ማዳበሪያን በመጠቀማችን ወጪን ከመቀነስ ባለፈ ምርታማነታችን እያሳደገልን ነው - አርሶ አደሮች
መቱ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በኢሉባቦር ዞን በቀያቸው አዘጋጅተው እየተጠቀሙ ያሉት የተፈጥሮ ማዳበሪያ ወጪ ከመቀነስ ባለፈ ምርታማነታቸውን እያሳደገ መሆኑን የዞኑ አርሶ አደሮች ገለጹ።
በኢሉአባቦር ዞን በበቾ ወረዳ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማምረት እየተጠቀሙ ካሉት አርሶ አደሮች መካከል ወይዘሮ አይናለም ጌታቸው አንዷ ናቸው።
ወይዘሮ አይናለም እንዳሉት፣ በግብርና ባለሙያዎች እገዛ ከአካባቢያቸው በሚገኙ ተረፈ ምርቶችና ዕፅዋት የተፈጥሮ ማዳበሪያ በማዘጋጀት መጠቀማቸው ከዚህ በፊት ለዘመናዊ ማዳበሪያ ይወጣ የነበረውን ወጪ ከማስቀረቱ በላይ የምርት መጠንን ማሳደጉን ገልጸዋል።
የዲዱ ወረዳ አርሶ አደሩ ገዳሙ አርፋሳ የተፈጥሮ ማዳበሪያን በማዘጋጀት ለእርሻ ሥራቸው እየተጠቀሙ መሆኑንና ከራሳቸው ፍጆታ አልፈው ለሌሎች በመሸጥ ተጨማሪ የገቢ ምንጭ እንደሆናቸው ተናግረዋል።
የተፈጥሮ ማዳበሪያው የመሬት ለምነትን ጠብቆ የሚያቆይ በመሆኑ፣ ምርታማነት ለዓመታት ቀጣይነት እንዲኖረው ያስችላል ብለዋል።
በበቾ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ተስፋዬ ዲቤሳ እንደተናገሩት በወረዳው የምርትና ምርታማነት ዕድገትን ለማረጋገጥ አርሶ አደሮቹን ተጠቃሚ ለማድረግ በተፈጥሮ ማዳበሪያ ዙሪያ በተሠራው ሥራ ውጤት እየመጣ ነው።
የኢሉአባቦር ዞን ግብርና ጽሕፈት ቤት ምክትል ኃላፊ ዳኜ ፍቅሬ እንደገለጹት በዞኑ በምርት ዘመኑ ከ265 ሺህ ኩንታል በላይ ዘመናዊ ማዳበሪያና ከ11 ሚሊየን ሜትር ኪዩብ በላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ እየዋለ ነው።
በዚህም የዞኑ አርሶ አደር ባለው መሬት ላይ የተፈጥሮ ማዳበሪያ አዘጋጅቶ በመጠቀም ውጤታማ እየሆነ መምጣቱን አንስተው፣ ልምድም እያዳበሩ ነው ብለዋል።
በወረዳዎቹ የተፈጥሮ ማዳበሪያ ማዘጋጃ ማዕከላት ተገንብተው ወደ ሥራ መግባታቸውን ጠቁመው ለአርሶ አደሮች እንዲደርስ መደረጉን ገልጸዋል።