ቀጥታ፡

ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በምርጥ ዘር አቅርቦትና በእጽዋት በሽታ ቁጥጥር ላይ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ ነው

ሮቤ፤ ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፡- መደ ወላቡ ዩኒቨርሲቲ የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በምርጥ ዘር አቅርቦትና በእጽዋት በሽታ ቁጥጥር ላይ ሙያዊ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አስታወቀ።

ዩኒቨርሲቲው በኩታገጠም አሰራር ለተደራጁ 120 አርሶ አደሮች የምርጥ ዘር ድጋፍ አድርጓል።

በመርሐግብሩ የዩኒቨርሲቲው የአካዳሚክ፣ የምርምርና የቴክኖሎጂ ሽግግር ምክትል ፕሬዚዳንት በዛብህ ወንድሙ (ዶ/ር) እንዳሉት ዩኒቨርሲቲው የአርሶ አደሩን ምርትና ምርታማነት ለማሳደግ በምርጥ ዘርና በእጽዋት በሽታ ቁጥጥር ላይ እየሰራ ነው።


 

ለዚህም ከባለድርሻ አካላት ጋር በመተባበር በምርምር ያወጣቸውን የተሻሻሉ የስንዴ ዝርያዎችና የግብርና አሰራሮችን ለአርሶ አደሩ እያስተዋወቀ መሆኑንም ጠቁመዋል።

ዩኒቨርሲቲው ከግብርና ምርምር ማዕከላት የተለቀቁ ምርጥ ዘሮችን በራሱና በአርሶ አደሩ ማሳ ላይ በማባዛት ለአርሶ አደሩ መልሶ እያሰራጨ መሆኑንም አመልክተዋል።

ይህም የአርሶ አደሮች ምርታማነት ከአንድ ሄክታር እስከ 80 ኩንታል ስንዴ ማምረት እንዳስቻለ አንስተዋል።

ዩኒቨርሲቲው የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የጀመረውን ስራ በማስፋት ከባሌ፣ ምሥራቅ ባሌና ምዕራብ አርሲ በኩታገጠም ለሚሰሩ ለተመረጡ 240 ለሚበልጡ አርሶ አደሮች ድጋፍና ክትትል እያደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

በዛሬው ዕለትም ከባሌ ዞን ለተመረጡ 120 አርሶ አደሮች የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ መደረጉ የጥረቱ አካልና ቀጣይነት ያለው መሆኑንም አመልክተዋል።

ዩኒቨርሲቲው አርሶ አደሩን በምርጥ ዘር አቅርቦትና ሌሎች የግብርና ድጋፎችን ከማድረግ በተጓዳኝ በእጽዋት በሽታ ቁጥጥር ላይ ተግባር ተኮር ሙያዊ ድጋፍ እየሰጠ መሆኑንም አመልክተዋል።


 

ድጋፉ ከተደረገላቸው አርሶ አደሮች መካከል ሐጅ ሁሴን አህመድ እንዳሉት በስንዴ ሰብል ልማት የመሳተፍ ረጅም ዓመት ልምድ ቢኖራቸውም ከምርጥ ዘር አጠቃቀም ልምድ ማነስ ምክንያት ከ25 ኩንታል የማይበልጥ የስንዴ እንደሚያመርቱ አስታውሰዋል።

በአሁኑ ወቅት ዩኒቨርሲቲው ያደረገላቸው የስንዴ ምርጥ ዘር ድጋፍ ምርታማነታቸውን ማሳደግ እንደሚያግዛቸው ገልጸዋል።


 

ዩኒቨርሲቲው ከምርጥ ዘር በተጓዳኝ በየጊዜው በሚያደርግላቸው ሙያዊ ድጋፍ ምርታማነታቸውን እንዳሳደገው የገለጹት ደግሞ ሌላው አርሶ አደር ሐጅ አማን ጎዳና ናቸው።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም