ቀጥታ፡

መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት የተቀላጠፈ አገልገሎት እንድናገኝ አስችሏል

ቦንጋ፤ ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፦ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ያልተገባ ወጪንና እንግልትን በማስቀረት የተቀላጠፈ አገልገሎት እንድናገኝ እያስቻለ ነው ሲሉ በቦንጋ ከተማ የማዕከሉ ተገልጋዮች ተናገሩ።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ተደራሽ በማድረግ ማህበረሰቡ በአቅራቢያው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት እንዲያገኝ በትኩረት እየተሰራ መሆኑ ተጠቁሟል።

በክልሉ ከሚገኙ ስድስት መሶብ የአንድ ማዕከላት መካከል አንዱ በሆነው የቦንጋ ማዕከል ሲገለገሉ ኢዜአ ያነጋገራቸው ዜጎች ከእንግልት የፀዳ ቀልጣፋና ግልፅ አገልግሎት እያገኙ መሆኙን ተናግረዋል።


 

አስተያየታቸውን ከሰጡት መካከል ነስረዲን ኑሩ እና ወጣት ሀይማኖት ታምሩ፤ በማዕከሉ አዲስ ንግድ ፈቃድን በአጭር ደቂቃና ፍጥነት ያለምንም እንግልት ማውጣታቸውን ነው የገለጹት።

ይህም ከዚህ ቀደም የነበረውን የተንዛዛ አሰራር በማስቀረት ጊዜያቸውን በአግባቡ መጠቀም እንዳስቻላቸው ጠቁመው፣ በቀጣይ ወደ ማዕከሉ ያልገቡ ተቋማትን በማካተት አገልግሎቱን ማስፋት እንደሚገባም ነው የተናገሩት።


 

ከዚህ ቀደም የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማግኝት ብዙ ምልልሶችና እንግልት እንደሚገጥመው ያነሳው ደግሞ ወጣት እምሩ መሸሻ ሲሆን፣ በአጭር ጊዜ ውስጥ በማዕከሉ ያለምንም እንግልት አገልግሎት ማግኘቱን ነው የተናግረው።

አሰራሩ ከእጅ መንሻ የፀዳ ግልፅና ፈጣን በመሆኑ ከዚህ ቀደም የነበሩ እሮሮዎችን በመፍታት እርካታን የጨመረ በመሆኑ አገልግሎቱን የማስፋት ስራ መጠናከር አለበት ነው ያለው።


 

የቦንጋ መሶብ የአንድ ማዕከል አልግሎት ዋና ስራ አስኪያጅ አወል አባገሮ ተበታትነው ይሰጡ የነበሩ አገልግሎቶችን በአንድ ማዕከል በመሰብሰብ ለህብረተሰቡ ፈጣን፣ ግልፅ እና ወጪ ቆጣቢ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ ነው ብለዋል።

በማዕከሉ  በድምሩ 8 የፌዴራል፣ የከተማ አስተዳደር እና የዞን ተቋማት ተለይተው 44 አገልግሎቶች በአንድ ማዕከል እየተሰጡ ሲሆን በቀጣይ አገልግሎቱን የማስፋት ስራ ይሰራል ብለዋል።

የማዕከሉ ባለሙያዎችም የአገልጋይነት መንፈስ ተላብሰው አገልግሎት እየሰጡ በመሆኑ የተገልጋዮች ቁጥር ከቀን ወደ ቀን እየጨመረ መምጣቱን ጠቁመዋል።


 

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ዋና አስተባባሪ አስራት አዳሮ በበኩላቸው፣ በመሶብ የአንድ ማዕከል የሚሰጡ አገልግሎቶች በተለይ ብልሹ አሰራሮችን ማስቀረት የሚያስችሉ ናቸው።

በመጀመሪያ ምዕራፍ የተገነባው የክልሉ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት እስካሁን ከ36 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች  አገልግሎት መስጠቱን ተናግረዋል።

ይህን ለማስፋት በተሰጠው ትኩረት አምስት ተጨማሪ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎቶች ተመርቀው ወደ ስራ መግባታቸውን ነው ያነሱት።

በአዲሱ በጀት ዓመትም ተጨማሪ 15 መሶብ የአንድ ማዕከላትን የመገንባት ስራ መጀመሩን ጠቁመው፣ ይህም ህብረተሰቡ ከስራው ሳይነጠል በአቅራቢያው ፈጣንና ቀልጣፋ አገልግሎት በአንድ ቦታ ማግኘት ያስችለዋል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም