በቢዝነስ ዲፕሎማሲ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋትና የቱሪዝም ዘርፉን ከማነቃቃት አኳያ አመርቂ ሥራዎች ተሰርተዋል - ኢዜአ አማርኛ
በቢዝነስ ዲፕሎማሲ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋትና የቱሪዝም ዘርፉን ከማነቃቃት አኳያ አመርቂ ሥራዎች ተሰርተዋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በቢዝነስ ዲፕሎማሲ ማዕቀፍ የኢንቨስትመንት ዕድሎችን ማስፋት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ እና የቱሪዝም ዘርፉን ከማነቃቃት አኳያ አመርቂ ሥራዎች መሰራታቸውን በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ገለጹ።
መንግሥት በሀገሪቱ ምጣኔ ሀብታዊ እንቅስቃሴ ውስጥ ያሉ ማነቆዎችን በመፍታት ወደ ተሻለ እድገት ጎዳና ለመጓዝ ከወሰዳቸው እርምጃዎች መካከል ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ይጠቀሳል።
እርምጃውም በሀገር ውስጥ በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ላይ የሚሳተፉ የሀገር ውስጥ ኢንቨስተሮችን ከመሳብ ባለፈ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ከመሳብ አኳያ አዎንታዊ ሚና እየተጫወተ ይገኛል፡፡
በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ጉዳዮች ዳይሬክተር ጄነራል አምባሳደር ዘሪሁን አበበ ለኢዜአ እንደገለጹት ኢትዮጵያ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን መሳብ የሚያስችል ምቹ መልከዓ ምድራዊና ኢኮኖሚያዊ አቅሞች ያላት ሀገር ናት፡፡
ነገር ግን ይህን ያላትን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ ማዋል የሚያስችሉ የአሰራር ስርዓቶችን በመዘርጋት ለሀገር ሁለንተናዊ የልማት እድገት ከማዋል አንጻር ክፍተቶች እንደነበሩ ተናግረዋል።
በሀገሪቱ ከዚህ ቀደም የነበሩ የፖሊሲ፣ የሕግና የፋይናንስ ማዕቀፎች ኢትዮጵያ ለውጭ ቀጥታ ኢንቨትመንት ምቹ አለመሆን እንደ ምክንያትነት አንስተዋል።
መንግሥት ችግሩን ለመፍታት በወሰዳቸው ሀገር በቀል የማክሮ የኢኮኖሚ ማሻሻያና መዋቅራዊ ለውጦች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በሀገሪቱ እንዲነቃቃ አቅም ፈጥሯል ብለዋል።
ኢትዮጵያ ለዓለም አቀፍ ቢዝነስ ምቹ መደላድል መፍጠሯ የውጭ ባለሀብቶችና ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስት ለማድረግ ያላቸው ፍላጎት እንዲያድግና የኢንቨስትመንት ፍሰት እንዲጨምር ማድረጉን አስታውቀዋል።
ከዚህም ባለፈ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ ምክንያት ከተለመዱት የኢንቨስትመንት ምንጮች በተጨማሪ ከአፍሪካ፣ ከገልፍ እና ከእስያ ሀገራት አዳዲስ ኢንቨስተሮች በስፋት በሀገራችን ኢንቨስት እያደረጉ መሆኑ አንዱ ማሳያ ነው ሲሉ ገልጸዋል።
ለአብነትም በናይጄሪያው ዳንጎቴ ኩባንያ በኩል በሲሚንቶ፣ በማዳበሪያና በሌሎች መስኮች ሰፊ የኢንቨስትመንት እንቅስቃሴ በኢትዮጵያ እየተከናወነ መሆኑን ጠቁመው የቴሌኮም ዘርፉም ለውጭ ኢንቨስትሮች ክፍት መደረጉን ተከተሎ የኬንያ ኩባንያዎች ወደ ሀገር ውስጥ መግባታቸውን አስታውቀዋል።
ከተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ከሳውዲ አረቢያ፣ ከኩዌት እና ቬይትናም የሚመጡ ባለሀብቶች በከፍተኛ ደረጃ መጨመሩን አንስተው በቬይትናም ኩባንያ የሚከናወነው የሶላር ፓናል ማምረት ስራ ለሀገሪቱ ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ እያስገኘ መሆኑንም አክለዋል።
የቢሾፍቱ ኢንተርናሽናል ኤርፖርት ግንባታ መጀመሩ በርካታ ግዙፍ ተቋማት ኢንቨስት ለማድረግ ፍላጎት እንዲያሳዩ በር መክፈቱንም አንስተዋል።
አምባሳደር ዘሪሁን አያይዘውም መንግሥት የውጭ ቀጥታ ኢንቨትመንትን ለመሳብ የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጥል ለንፋስ ኃይል፣ ለተፈጥሮ ጋዝ ልማት፣ ለፋርማሲዩቲካል፣ ለግብርና እና ለማምረ ዘርፎች ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ሀሳብ አመንጪነት በገበታ ለሀገር ኢንሼቲቭ የተገነቡ የቱሪዝም መሰረተ ልማቶች እንዲሁም በቡና ምርት ላይ የመጡ መዋቅራዊ ለውጦች በርካታ ጎብኚዎችንና ኢንቨስተሮችን እየሳቡ አንደሚገኙ ገልጸዋል።
ኢትዮጵያውያን ከሀገር ውጭ ኢንቨስት በማድረግ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሬ የሚያገኙበት አሰራር መዘርጋቱ ሀገሪቱ ያላትን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያሳድግ መሆኑን አመልክተዋል።
ሚኒስቴሩም ከቀደሙት ዋና ዋና ተልዕኮዎቹ መካከል የቢዝነስ ዲፕሎማሲ ግንባር ቀደሙ ነው ብለዋል።
ተልዕኮውን እውን ለማድረግም የሀገሪቱን የኢንቨስትመንት እድሎች በማስተዋወቅ፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት በመሳብ፣ ለሀገር ውስጥ ምርቶች የውጭ ገበያ በማፈላለግና የቱሪዝም ዘርፉን በማሳደግ በኩል ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ ነው ብለዋል።
በዚህም ድርጅቶችና ግለሰቦች ሀገሪቱን እንዲጎበኙ ከማመቻቸት ጀምሮ፣ ጉብኝቱን ተከታትለው ኢንቨስት እንዲያደርጉ የማነሳሳትና የማግባባት ስራዎችን በከፍተኛ ደረጃ እየሰራ እንደሚገኝ በዚህም ተጨባጭ ለውጦች እየታዩ መሆኑ አመልክተዋል።
በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት 4 ነጥብ 32 ቢሊየን ዶላር የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት ወደ ሀገር ውስጥ መሳብ መቻሉን ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።