ቀጥታ፡

በክልሉ በኮንስትራክሽንና የከተማ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች የብድር ተጠቃሚ ሆነዋል

ባህር ዳር፤ ሐምሌ 17/2018(ኢዜአ)፦ በአማራ ክልል በኮንስትራክሽንና የከተማ ግብርናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች የስራ እድል የተፈጠረላቸው ዜጎች የብድር ተጠቃሚ መሆናቸውን የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ አስታወቀ።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በሥራ ዕድል ፈጠራና በባለሙያዎች ብቃት ምዘና ማረጋገጫ ተግባራት አፈጻጸም ላይ ያተኮረ መግለጫ ዛሬ ተሰጥቷል።

የክልሉ ሥራና ክህሎት ቢሮ ምክትል ኃላፊ አማረ ዓለሙ እንደገለጹት፤ ቢሮው በሰው ሀብት ልማት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራና በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ላይ በማተኮር ሲሰራ ቆይቷል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት በተከናወነው ቅንጅታዊ ስራ ከ1 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን ገልጸዋል።

የሥራ ዕድል ከተፈጠረላቸው ወገኖች መካከል ከ986 ሺህ 670 በላይ የሚሆኑት ቋሚ የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ሲሆኑ፣ ቀሪዎቹ ደግሞ ጊዜያዊ የሥራ ዕድል የተፈጠረላቸው ናቸው።

የሥራ ዕድሉን መፍጠር የተቻለውም በኮንስትራክሽን፣ በከተማ ግብርና፣ በአገልግሎት፣ በእንጨትና ብረታብረት ሥራ እና በሌሎች የዕድገት ተኮር ዘርፎች መሆኑን አመላክተዋል።

ለሥራ ዕድል ተጠቃሚዎች 3 ቢሊየን ብር ብድር ለማቅረብ ታቅዶ ከእቅድ በላይ ከ10 ነጥብ 9 ቢሊየን ብር በላይ ማሰራጨት ተችሏል ብለዋል።

በዚህም የነበረባቸውን የመሥሪያ ገንዘብ ችግር ለመቅረፍ ተሞክሯል ያሉት ምክትል ኃላፊው የመሥሪያና የመሸጫ መሬት እንዲሁም ሼድ መስጠት መቻሉንም ጠቁመዋል።

በበጀት ዓመቱ በተደረገው የተጠናከረ ድጋፍና ክትትል ከ15 ሺህ 700 በላይ ኢንተርፕራይዞች የደረጃ ሽግግር ማድረጋቸውን አብራርተዋል።

የአማራ ክልል የሙያ ብቃትና ምዘና ማረጋገጫ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ተስፋዬ የሺዋስ በበኩላቸው፤ በበጀት ዓመቱ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙ ሙያተኞችን ብቃት ማረጋገጥ ላይ በማተኮር መሰራቱን ገልጸዋል።

በዚህም በኮሌጆች በዲፕሎማ ደረጃ የሠለጠኑ ከ224 ሺህ በላይ ዜጎች የብቃት ምዘና እንዲወስዱ ተደርጎ፣ ከ70 በመቶ በላይ የሚሆኑት ምዘናውን በማለፍ የማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ይህም ለአምራች ኢንዱስትሪዎችና ለሌሎች የኢንቨስትመንት ዘርፎች ብቃት ያለው የሰው ሀብት በማቅረብ የተጀመረው ዕድገት ተጠናክሮ እንዲቀጥል የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም