ቀጥታ፡

በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ118 ሺህ የሚበልጡ ዜጎች የስራ ዕድል ተጠቃሚ ሆነዋል

ጭሮ ፤ሐምሌ 17/2018 (ኢዜአ)፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ሐረርጌ ዞን በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ118 ሺህ የሚበልጡ  ዜጎችን የስራ እድል ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን የዞኑ ስራ ዕድል ፈጠራ ጽህፈት ቤት ገለፀ።

የሥራ ዕድሉ ተጠቃሚዎችም በመንግሥት በተመቻቸላቸው የብድርና የማምረቻ ቦታ በመታገዝ ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልጸዋል።

የጽሕፈት ቤቱ የዕቅድ ዝግጅት እና ክትትል ቡድን መሪ አቶ አሸብር ደበበ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፤ ጽሕፈት ቤቱ በ8 ሺህ 801 ማኅበራት ለተደራጁ 118 ሺህ 500 ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል መፈጠሩን አስረድተዋል።

ለዚህም ስኬታማነት የመሬት ዝግጅት፣ የብድር አቅርቦትና የስልጠና አገልግሎት በመስጠት ዜጎችን ወደ ሥራ ማስገባት ተችሏል ብለዋል።

ከተፈጠረው የሥራ መስክ መካከል ግብርና፣ የእንስሳት እርባታና ማድለብ፣ ንብ ማነብ፣ የዶሮ እርባታ፣ የጥቃቅንና አነስተኛ ንግድና ሌሎችም እንደሚገኙበት አመላክተዋል።

በእንቅስቃሴያቸው ውጤታማ እንዲሆኑም በገጠርና በከተሞች በ3 ሺህ 200 ማኅበራት ለተደራጁ ወጣቶች 4 ሺህ 335 ሄክታር የእርሻና የመስሪያ ቦታ መሰጠቱን ጠቁመዋል።

የመነሻ ካፒታል እጥረት እንዳያጋጥማቸውም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ብድር መንግሥት ማመቻቸቱን አስታውቀዋል።

ከወሰዱት ብድር ውሰጥ እስካሁን ድረስ ከ65 ሚሊዮን ብር በላይ የሚሆነው ተመላሽ ማድረግ መቻላቸውን ተናግረዋል።

ለምርቶቻቸውም ከተለያዩ ተቋማት እና ድርጅቶች 3 ቢሊዮን ብር የሚጠጋ የገበያ ትስስር በመፍጠር ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተደራጅተው በዶሮ እርባታ የተሰማሩት አቶ አሰበ ተስፋዬ እንዳሉት፤ በተመቻቸላቸው የመስሪያ ቦታና ብድር በመታገዝ በመጀመሪያው ምዕራፍ 600 እንቁላል ጣይ ዶሮዎችን እያረቡ ይገኛሉ።

አሁን ላይ የእንቁላል ምርቱን በተመጣጣኝ ዋጋ ለገበያ በማቅረብ ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

በቦኬ ወረዳ ቦኬ ጥቃ ከተማ በእንስሳት ማድለብ ከጓደኞቹ ጋር  የተሰማራው ወጣት ሀብታሙ ዓለሙ በበኩሉ፤ ባገኙት 500 ሺህ ብር ብድር የመነሻ ካፒታል የጀመሩት ሥራ ውጤታማ እያደረጋቸው ይገኛል።

ሰንጋዎችን በማድለብ ከአካባቢው ገበያ ባለፈ ለጭሮ እና በዴሳ ሉካንዳ ነጋዴዎች በማቅረብ ትርፋማ መሆናቸውን ነው የገለፀው።

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም