ቀጥታ፡

ምክክር ለዘላቂ ሰላምና ለጠንካራ ሀገረ-መንግሥት ግንባታ መሠረት

ኢትዮጵያ በረጅም ታሪኳ በርካታ የፖለቲካ ሥርዓቶችን፣የሀገር አመራርና ማህበራዊ ለውጦችን ብታሳልፍም፣ባለፉት ዘመናት የተከማቹ ቅሬታዎች፣ የፖለቲካ አለመግባባቶችና የተለያዩ ትርክቶች በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት ላይ ከባድ ጫና ፈጥረዋል።

እነዚህ ችግሮች በተለያዩ ጊዜያት የሰው ሕይወት እንዲጠፋ፣የንብረት ውድመት እንዲከሰት፣ የሀገር አንድነት እንዲዳከምና ሀገራዊ እድገት እንዲዘገይ አድርገዋል።

ባለፉት ጊዜያት እነዚህን ልዩነቶችን በሰላማዊ መንገድ ለመወያየትና ለመፍታት የሚያስችል የጋራ ሀገራዊ መድረክ አለመኖሩ እንደ ሀገር ዋጋ አስከፍሎን ቆይቷል።

ሀገራዊ ምክክር ብቸኛው ዘላቂ የሰላም ጎዳና ስለመኾኑ በተለያዩ ጊዜያት በሀገር ወዳድ ዜጎች ምክረሀሳብ ቢቀርብም፣ሰሚ ጆሮ ሳያገኝ በመቅረቱ ያለመግባባት መንስኤዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል።

የፖለቲካ ልዩነቶች ሳይፈቱ ሲቀሩ በሀገር ውስጥ የሚፈጠረው አለመተማመን የሁሉንም ዜጎች ሕይወት ይነካል።

ለዚህም ነው ሀገራዊ ምክክር እንደ አስፈላጊ የሰላም ግንባታና የጋራ መግባባት መሣሪያ የሚታየው።

ሀገራዊ ምክክር የተለያዩ ሐሳቦችንና ፍላጎቶችን ለማጥፋት ሳይሆን፣ልዩነቶችን በማክበር በጋራ ለመፍታት የሚያስችል ሂደት ነው።

የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች፣ማህበረሰቦች፣ ምሁራን፣ የፖለቲካ አካላትና የህብረተሰብ ተወካዮች በአንድ ጠረጴዛ ዙሪያ ተቀምጠው ለሀገር ችግሮች ዘላቂ መፍትሄ ለመፈለግ የሚያደርጉት ጥረት ዘላቂ አንድነትና ሰላምን ያመጣል።

ሀገር የምትፀናው በአንድ ወገን ሐሳብ የበላይነት ብቻ ሳይሆን፣ የተለያዩ ሐሳቦችን በማስተባበርና የሁሉንም ድምፅ በማክበር ነው።

ይህ ምክክር በቅድሚያ የሚጠይቀው ለመስማትና ለመደማመጥ ፈቃደኛ መሆንን ነው። ሌላውን ለመረዳት፣ የተለያዩ ሐሳቦችን ለማክበርና በጋራ ጥቅም ላይ ለመስማማት ዝግጁ መሆን ያስፈልጋል።

ሀገራዊ ምክክር በተሳካ ሁኔታ ሲካሄድ የተፈጠሩ ታሪካዊ ቁስሎችን ለመፈወስ፣ የተለያዩ አካላት እርስ በርስ እንዲተማመኑና የሀገር የጋራ አቅጣጫ እንዲገለጽ በማድረግ ለዘላቂ ሰላም ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል።

ሰላም ከሌለ ሀገራዊ የልማት ትልሞች በተሟላ ሁኔታ ሊፈጸሙ አይችሉም፤ ምክክር ግን ለሰላም መሠረት የሚሆንና ሀገርን በፅኑ የሚያቆም የመተማመን ድልድይ ይገነባል።

የኢትዮጵያ ሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን ዋናው የምክክር ጉባኤን ሐምሌ 08 ቀን 2018 ዓ.ም በአዲስ አበባ አዲስ ዓለም አቀፍ ኮንቬንሽን ማዕከል በይፋ መጀመሩ ይታወሳል።

በዚህም በሀገር ውስጥና በውጭ ያሉ ኢትዮጵያዊያንን በማወያየት ምክክር የሚደረግባቸው ስምንት አጀንዳዎችን ምክክር እየተደረገ ይገኛል።

የዋናው ሀገራዊ የምክክር ጉባኤ ተመካካሪዎችም ያለምንም ገደብ የሃሳብ መቀራረብንና የጋራ መግባባትን በማጎልበት የኢትዮጵያን ብሩህ ተስፋ የሚገነባ ምክክር እያደረጉ መሆኑን ገልጸዋል።

ሀገራዊ ምክክር የጋራ አሸናፊነት ማብሰሪያ፤ለጠንካራ ሀገረ መንግሥት ግንባታ ማሳለጫ መሆኑን ተሳታፊዎች አክለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም