ቀጥታ፡

የቱሪዝም ዘርፍ በመደመር ዕይታ፦ ሌላው የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ምሰሶ

ቱሪዝም በዓለም አቀፍ መድረክ ትርጉም ያለው ቦታ አለው፡፡የምሥራቅና የምዕራብ ኢኮኖሚ መመጣጠን የቱሪስቱን ብዛትና ዓይነት ጨምሯል፡፡ለቱሪዝም ያለን ሀገራዊ ዕምቅ ዐቅማችንም ከፍተኛ ነው።ይህንን በመረዳት በሀገር በቀል የኢኮኖሚ ሪፎርም ውስጥ ከተቀመጡት አምስቱ ዓምዶች መካከል አንዱ እንዲሆን አድርገናል።

ኢንዱስትሪው በሀገራችን ኢኮኖሚያዊ፣ ማኅበራዊማ አካባቢያዊ ሁኔታዎች ውስጥ ትልቅ አስተዋጽዖ እንዲኖረው እንፈልጋለን፡፡የመጣውን መልካም ዕድል ወደሚጨበጥ ጥቅም ለመቀየር፣ ባለፉት ጥቂት ዓመታት፣ በፈጠራ እና በተግባራዊ ፍጥነት በርካታ መዳረሻዎችን አልምተናል፡፡ በከተማና በገጠር የሚገኙ የቱሪዝም መዳረሻዎችን አቀናጅተናል፡፡እንዲሁም ነባር የጎብኚ መዳረሻዎችን አሻሽለናል፡፡ አዳዲስ መዳረሻዎችንም አልምተናል፡፡እነዚህ ሁሉ በተለየ ትኩረት ከሠራንባቸው የለውጥ ማሳያዎቻችን መካከል ጥቂቶቹ ናቸው፡፡


 

ሀገራችን ከዚህ በፊት ከነበራት የጎብኚ መዳረሻዎች ላይ በእነዚህ ጥቂት ዓመታት ብዙ ጨምረናል።መዳረሻዎቹም መላው ሀገራችንን ያካለሉ ናቸው። ከሀገራችን ስፋትና ከሀብት እጥረት አንጻር ያልደረስንባቸውና በዕቅድ ላይ ያሉ ብዙ መዳረሻዎችም በቀጣይ ይገነባሉ።

በእጃችን ላይ ያሉ የጎብኚ መዳረሻዎችን በአግባቡ አገልግሎት ላይ ማዋልና ከዚህም ሊገኝ የሚችለውን ሀገራዊ ጥቅም ሁሉ መሰብሰብ ተገቢና በቀጣይ ለምንጓዘው አቅጣጫ ትልቅ ግብአት የሚሆን ነው።ከዚህ አንጻርም ብዙዎቹን በፍጥነት ወደ ሥራ አስገብተናል። ትሩፋቶቹንም እያጣጣምን እንገኛለን።

በእነዚህ ጥረቶች ምክንያት ሀገራችንን የሚጎበኙ የውስጥም ይሁን የውጭ ጎብኚዎች ቁጥር በጥሩ ሁኔታ እያደገ ነው። ይሁንና ዘርፉ ከፍተኛ ዕድገት እንዲያስመዘግብ ገና ብዙ መሥራት ይጠበቅብናል።

ሀገራችን ከቱሪዝም ልታገኛቸው የምትችላቸውን ማኅበራዊ፣ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና አካባቢያዊ ጥቅሞች ሁሉ ከቀረው ዓለም ጋር ተወዳድራ እንድታገኝ፤ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ጎብኚ ወደ ሀገራችን መሳብ አለብን። ለዚህም የተለያዩ ስልታዊ መላዎችን (Strategies) ነድፈን እየተንቀሳቀስን እንገኛለን።

የመደመር መንግሥት መፅሐፍ ከገጽ 272 - 273

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም