ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ታሪካዊውን የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክን ጎበኙ - ኢዜአ አማርኛ
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ታሪካዊውን የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክን ጎበኙ
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፦ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ በጋና አክራ ከተማ የሚገኘውን ታሪካዊውን የክዋሜ ንክሩማህ መታሰቢያ ፓርክን ጎብኝተዋል።
በሐውልታቸው ሥርም የአበባ ጉንጉን አኑረዋል።
ይህ ስፍራ የጋና የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት እና የፓን-አፍሪካኒዝም አቀንቃኝ የዶክተር ክዋሜ ንክሩማህ እንዲሁም የባለቤታቸው የፋቲያ ንክሩማህ መካነ መቃብርና ታሪካዊ ሙዚየምን ያካተተ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በመልዕክታቸው ላይ አስፍረዋል።
ጋናውያን ለአፍሪካ ነፃነትና አንድነት አቀንቃኙ መሪያቸው ግዙፍ ሐውልት መታሰቢያ መገንባታቸው የቀደሙትን ማክበር ለትውልድና ለሀገር ግንባታ ያለውን ሚና ያሳያል ብለዋል።
ዶ/ር ክዋሜ ንክሩማህ ለጋና ነፃነት ብቻ ሳይሆን፣ ሙሉ አፍሪካ ከቅኝ ግዛት ነፃ እንድትወጣ የነበራቸው ራዕይ ዛሬም ድረስ ለትውልዱ ትልቅ የብርታት ምንጭ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይም ከኢትዮጵያ ጋር የነበራቸው ጥብቅ ወዳጅነት እና ለአፍሪካ አንድነት ድርጅት (የአሁኑ አፍሪካ ኅብረት) መመስረት ያበረከቱት አስተዋጽኦ ሁልጊዜም በክብር የሚታወስ መሆኑን ጠቅሰዋል።