የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ ነው
ጂንካ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፡- የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ከመደበኛ ሥራው ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ ገለጹ።
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በዘንድሮው የክረምት ወራት በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፣ በአሪ እና በደቡብ ኦሞ ዞኖች ለሚገኙ አረጋውያን እና አቅመ ደካሞች መኖሪያ ቤቶችን እንዲሁም ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባት ሥራ ጀምሯል።
የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የተሰጠውን ኃላፊነት በአግባቡ ከማከናወን ጎን ለጎን ማኅበራዊ ኃላፊነቱንም እየተወጣ ይገኛል።
ተቋሙ በተያዘው ክረምት ከሚያከናውናቸው የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሥራዎች መካከል በጂንካ ከተማ የአቅመ-ደካማ እናትን ቤት እድሳት እንዲሁም በአንድ ትምህርት ቤት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍል ግንባታን በማስጀመር ወደ ሥራ ገብቷል ብለዋል።
በተጨማሪም በከተማዋ ለሚገኙ 60 ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁሶችን ማበርከት የተቻለ ሲሆን የችግኝ ተከላ መርሃ-ግብር መከናወኑን ገልጸዋል።
የተቋሙ ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ሞገስ መኮንን በበኩላቸው፤ ተቋሙ በክረምቱ የበጎ ፈቃድ መርሃ-ግብር በደቡብ ኦሞ እና በአሪ ዞኖች የሰባት አረጋውያንና አቅመ-ደካሞችን ቤቶች ገንብቶ እንደሚያስረክብ ተናግረዋል።
ከዚህ በተጨማሪም በሁለቱም ዞኖች ሰባት ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን የመገንባት እና የትምህርት ቁሳቁስ የማቅረብ ሥራ እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የጂንካ ከተማ ከንቲባ አቶ ደግፌ ጌታቸው የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል በከተማው ለሚገኙ አቅመ ደካሞች እና አረጋውያን ላደረገው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።
በትምህርት ቤቶች የተጀመረው አዳዲስ የመማሪያ ክፍሎች ግንባታም የመማሪያ ክፍል እጥረቱን ለመቅረፍ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለው ጠቁመው፣ ዛሬ የመሠረተ ድንጋይ የተቀመጠላቸው ግንባታዎች እስኪጠናቀቁ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።