በጋምቤላ ክልል የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በጋምቤላ ክልል የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ
ጋምቤላ ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፡- የጋምቤላ ክልልን የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ ገለጹ።
የክልሉ አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የ2018 በጀት ዓመት የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ዛሬ በጋምቤላ ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድሯ ወይዘሮ ዓለሚቱ ኡሞድ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ያጋጠሙ ፈተናዎችን በመቋቋም የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን ገልጸዋል።
በተለይም በማዕድን፣ በእንስሳት ሀብት ልማት እንዲሁም በሌሎች የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፎች የተመዘገቡት ውጤቶች ተስፋ ሰጪ ናቸው ብለዋል።
ከዚሁ ጎን ለጎን በክልሉ የሌማት ትሩፋት ኢኒሼቲቭን በማስፋት የሕዝቡን ሕይወት ለማሻሻል የተከናወኑ ሥራዎች ውጤታማ እንደነበሩ ጠቁመዋል።
በቀጣይም ዘርፉን ይበልጥ በማጠናከር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የተቀመጠውን ግብ ለማሳካት ያላሰለሰ ጥረት ይደረጋል ብለዋል።
በተለይም የክልሉን የሕዝቡን ሁለንተናዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተጀመሩ አበረታች ተግባራት በተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ጠቅሰው፣ ወጪ ቆጣቢ የአሰራር ስርዓትን ተግባራዊ በማድረግ ለልማትና ለመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ተገቢው ምላሽ ይሰጣልም ብለዋል።
የክልሉ ፕላንና ልማት ቢሮ ምክትል ኃላፊ ወይዘሮ ገነት ኤሊያስ በበኩላቸው፤ ቢሮው የልማትና የመልካም አስተዳደር ዕቅዶችን በመንደፍ የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በትኩረት እየሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በበጀት ዓመቱ የታቀዱ ተግባራትን በየደረጃው በመገምገም የተሻለ አፈጻጸም እንዲመዘገብ የማስቻል ሥራ ሲሠራ መቆየቱንም አብራርተዋል።
በዚሁ የዕቅድ አፈጻጸም ግምገማ መድረክ ላይ የክልሉ የሴክተር መሥሪያ ቤት ኃላፊዎችና ከፍተኛ ባለሙያዎች ተሳትፈዋል።