በክልሉ የትራፊክ እንቅስቃሴ መረጃን መሰብሰብ የሚያስችል የዲጅታል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የትራፊክ እንቅስቃሴ መረጃን መሰብሰብ የሚያስችል የዲጅታል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ ነው
ወላይታ ሶዶ፣ ሀምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የትራፊክ እንቅስቃሴ መረጃን መሰብሰብ የሚያስችል የዲጅታል አሰራር ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።
በክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን የትራፊክ አደጋ መከላከልና ፍሰት ቁጥጥር ዳይሬክተር ኮማንደር ለማ ላቾሬ ለኢዜአ እንደገለጹት በተጠናቀቀው በጀት አመት የትራፊክ አደጋን ለመከላከልና ለመቀነስ በርካታ ተግባራት ተከናውነዋል፡፡
በትምህርት ቤቶች፣ በእምነት ተቋማት እና ህዝብ በሚሰበሰብባቸው አካባቢዎች የግንዛቤ ማስጨበጫ ትምህርት መስጠትና የትራፊክ ህግን በአግባቡ መተግበር ከተሰሩ ስራዎች መካከል ዋነኞቹ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።
የትራፊክ አደጋ በስፋት በሚከሰትባቸው ጋሞ፣ ወላይታ እና ጌዴኦ ዞኖች ተለይተው ቴክኖሎጂን በመጠቀም የትራፊክ ፍሰትና አደጋ ቁጥጥር ስራ መከናወኑን አመልክተዋል።
በወላይታ ሶዶ ከተማ በካሜራ የተደገፈ የትራፊክ አደጋ መረጃ መሰብሰቢያ ሲስተም ተግባራዊ መደረጉን ገልጸው አርባምንጭና ዲላ ከተሞችም ተግባራዊ ለማድረግ ጥናት መጠናቀቁን ተናግረዋል።
ይህም በአንድ ማዕከል የትራፊክ ፍሰት ቁጥጥር በማድረግ የመረጃ አያያዝ ስርዓቱን ዘመናዊና ቀልጣፋ ማድረጉን ጠቁመዋል።
በኮሚሽኑ የትራፊክ አደጋ መረጃ እና ስታቲስቲክስ ዲቪዥን ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር ታደለ አበራ በበኩላቸው በክልሉ በቴክኖሎጂ የታገዘ የትራፊክ አደጋ የመመዝገብና የመተንተን ስራ እየተከናወነ በመሆኑ የቁጥጥርና የክትትል ስራውን ቀልጣፋ ማድረጉን ተናግረዋል።
በከተማው በዲጂታል አሰራር የታገዘ የትራፊክ አደጋ የክትትልና የቁጥጥር ተግባር እየተከናወነ መሆኑን የገለጹት ደግሞ በወላይታ ሶዶ ከተማ ፖሊስ መምሪያ የትራፊክ አደጋ ቁጥጥር ዲቪዥን ኃላፊ ረዳት ኢንስፔክተር ዝናቡ ገዛኸኝ ናቸው።
በከተማው የተጀመረው የካሜራ ቴክኖሎጂ በዘርፉ አሰራሩን እያዘመነው መሆኑንም አስታውቀዋል።