ቀጥታ፡

በጋምቤላ ክልል ከ7 ሺህ 98 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ሆኗል

ጋምቤላ፤ ሀምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በጋምቤላ ክልል  በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ከ7 ሺህ 98 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ መደረጉን የክልሉ ማዕድን ቢሮ አስታወቀ። 

‎የጋምቤላ ክልል ማዕድን ቢሮ ኃላፊ አቶ ቻም ኡበንግ ለኢዜአ እንደገለጹት በክልሉ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት  በዘርፉ በተከናወኑ ተግባራት ስኬታማ ውጤቶች ተመዝግበዋል።

‎በበጀት ዓመቱ 6 ሺህ ኪሎ ግራም ወርቅ ለብሔራዊ ባንክ ገቢ ለማድረግ ታቅዶ ከ7 ሺህ 98 ኪሎ ግራም በላይ ወርቅ  ገቢ መደረጉን ተናግረዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ ገቢ የተደረው የወርቅ ምርት ከእቅዱ በ1 ሺህ 98 ኪሎ ግራም ብልጫ ያለው ሲሆን ከቀዳሚው ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በ1 ሺህ 669 ኪሎ ግራም ብላጫ ያለው መሆኑን ገልጸዋል።

‎ለተመዘገበው ውጤት መንግስት ለዘርፉ በሰጠው ትኩረት የቁጥጥር፣ የክትትልና የድጋፍ ስራዎች ተጠናክረው በመከናወናቸው መሆኑን ተናግረዋል።

በክልሉ በበጀት ዓመቱ በተከናወነው የማዕድን ሃብት ልማት ከ6 ሺህ 890 በላይ ዜጎች ቋሚና ጊዜያዊ የስራ እድል የተፈጠረላቸው መሆኑንም የቢሮ ሃላፊው ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም