ቀጥታ፡

በሲዳማ ክልል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ የፍራፍሬ ልማት ስራዎች እየተካሔዱ ነው

ሃዋሳ፤ ሃምሌ 16/2018 (ኢዜአ)፡- በሲዳማ ክልል አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ያደረጉ የፍራፍሬ ልማት ስራዎች እየተከናወኑ መሆኑን የክልሉ ቡና ፍራፍሬና ቅመማ ቅመም ልማት ባለስልጣን አስታወቀ፡፡

የባለስልጣኑ ዋና ዳይሬክተር አቶ መስፍን ቃሬ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ፤በክልሉ የምግብ ዋስትናን የሚያረጋግጥና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ፍራፍሬዎችን በማልማት የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተችሏል።


 

በክልሉ ካለው የፍራፍሬ ማሳ 43 ከመቶው በአቮካዶ ተክል የተሸፈነ ሲሆን የአፕልና አናናስ ተክልም የቤተሰብ ብልጽግና ፓኬጅ አካል ሆኖ  እየተሰራበት ይገኛል ነው ያሉት።

በአሁኑ ወቅትም በአቮካዶ ልማት የተሳተፉ ከ40 ሺህ በላይ አርሶ አደሮች ምርታቸውን ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪ ፓርክ ዘይት አምራች ፋብሪካዎች እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ 

ለዚህም በየዓመቱ የተሻሻሉ ችግኞች በመትከል ምርታማነትን የማሳደግ ስራ እየተከናወነ ሲሆን በተያዘው ዓመትም የ4 ነጥብ 5 ሚሊዮን ችግኞች ተከላ መጀመሩን ተናግረዋል፡፡

በክልሉ የጣራሜሳ አካባቢ አትክልትና ፍራፍሬ አምራችና አቅራቢ መሰረታዊ ህብረት ስራ ማህበር ሰብሳቢ አቶ ኩዬሬ ሁሬሳ፤ በአቮካዶ ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታችንን እያረጋገጥን ነው ብለዋል፡፡

በ2011 ዓ.ም 320 አርሶ አደሮችን በማቀፍ የተመሰረተው ማህበሩ፤በዋናነት ከአቮካዶ ምርት በተጨማሪ ቲማቲም፣ ጥቅል ጎመንና ሌሎች አትክልቶችን ከማምረት ባሻገር ችግኞችንም እንደሚያፈሉ ነው የተናገሩት።

ማህበራቸውን ወክለው ጣሊያን ሃገር በተካሄደ አውደ ርዕይ በመሳተፍም የገበያ ትስስር ለመፍጠር እንደቻሉም ነው የሚገልጹት።

በአሁኑ ወቅም በዓመት ሁለት ጊዜ የሚሰበስቡትን የአቮካዶ ምርት ለይርጋለም የተቀናጀ የግብርና ምርቶች ማቀነባበሪያ ኢንደስትሪ ፓርክ እያቀረቡ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ከ200 ሺህ ኪሎ ግራም በላይ የአቮካዶ ምርት ለማቅረብ ማቀዳቸውን የጠቆሙት አርሶ አደሩ፤ ለተከላ የሚሆኑ ከ10 ሺህ በላይ የተሻሻሉ የአቮካዶ ችግኞችን ለአካባቢው አርሶ አደሮች ማሰራጨታቸውን ተናግረዋል፡፡

 

 

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም