የቅርስ መገኛ ስፍራዎች ጥበቃን ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል - ኢዜአ አማርኛ
የቅርስ መገኛ ስፍራዎች ጥበቃን ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ማዋል ይገባል
ጎንደር፤ሐምሌ 16 /2016 (ኢዜአ)፡-የቅርስ መገኛ ስፍራዎች ጥበቃን ከአረንጓዴ አሻራ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለዘርፈ በዙ ጠቀሜታ ማዋል እንደሚገባ የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው ገለጹ።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን በጎንደር ከተማ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር አካሂዷል።
ዋና ዳይሬክተሩ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው እንደገለጹት፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርን ከታሪክና የባህል እሴቶች ልማት ጋር ማጣጣም ዘላቂ እድገትን ለማስመዝገብ ያለው ድርሻ የጎላ ነው።
የዚሁ አካል የሆነውና በጎንደር ከተማ የተተገበረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ቅርስ መገኛ ስፍራዎች ጥበቃን ከአረንጓዴ ልማት ጋር በማስተሳሰር ለዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ እንዲውሉ ለማስቻል መሆኑን አስረድተዋል።
ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ ቅርሶችን ከአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር ጋር ማስተሳሰር የአገርን እድገት ለማፋጠን አጋዥ ነው ብለዋል።
ባለስልጣን መስሪያ ቤቱ የተተከሉ ችግኞች ጸድቀው ለጥቅም እንዲበቁ በጀት በመመደብ ጭምር አስፈላጊውን እንክብካቤና ጥበቃ እንደሚያደርግ አስረድተዋል።
"ዛሬ የምንተክላቸው ችግኞችና የምንሰራቸው ተግባራት የዕለት ችግር መፍቻ ብቻ ሳይሆኑ፣ ለትውልድ የታሪክ፣ የተፈጥሮና የእውቀት ሀብቶች ናቸው" ሲሉ ጠቁመዋል።
የጎንደር ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ወይዘሮ ደብሬ የኋላ በበኩላቸው፤ በከተማዋ የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በከፍተኛ ትኩረት እየተካሄደ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
በዘንድሮው ክረምት በሚካሄደው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብርም ህብረተሰቡንና አጋር ተቋማትን ያሳተፈ የችግኝ ተከላ ተግባር ተጠናክሮ መቀጠሉን አስረድተዋል።
የሚተከሉ ችግኞችም ለውበትና ለደን ከሚሆኑት በተጨማሪ የህብረተሰቡን ዘላቂ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ ለፍራፍሬና ለቡና ተክሎች ልዩ ትኩረት በመስጠት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
በዕለቱም የቅድመ-አንደኛ ደረጃ መማሪያ ክፍል ግንባታ የመሰረት ድንጋይ የማስቀመጥና የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ የማድረግ ተግባራት ተከናውነዋል።
በችግኝ ተከላው ላይ ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌውን ጨምሮ የባለስልጣኑ ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች፣ የማኔጅመንት አባላትና የጎንደር ከተማ አስተዳደር ባለስልጣናት ተገኝተዋል።