ቀጥታ፡

የባሕርዳር ከተማን የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገ ነው

ባህርዳር፤ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፡-የባህር ዳር ከተማ የልማትና እድገት የተሞክሮ ማዕከል ለማድረግ ርብርብ እየተደረገ መሆኑን የአማራ ክልል ከተማና መሰረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ ሞላ መልካሙ(ዶ/ር) ገለጹ።

የባህርዳር ከተማ አስተዳደር የከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ የተጠናቀቀው በጀት ዓመት አፈጻጸምን የሚገመግምና የአዲሱ በጀት ዓመት እቅድ ትውውቅ መድረክ ዛሬ አካሂዷል።


 

የቢሮ ኃላፊው ሞላ መልካሙ(ዶ/ር) እንደገለጹት በክልሉ የሚገኙ በርካታ ከተሞችን ለንግድ፣ ቱሪዝምና ለኑሮ የተመቹ ለማድረግ ሁለገብ የልማት ስራ እየተከናወነ ይገኛል።

የኮሪደር ልማትን ጨምሮ ሌሎች የመሰረተ ልማት ግንባታዎችን በማከናወን ውብ፣ ሳቢና ማራኪ ለማድረግ በትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

የባህር ዳር ከተማ በሰፋፊ የአስፋልት መንገዶች፣ በኮሪደር ልማት፣ በስማርት ሲቲ ትግበራ፣ የአረንጓዴ ልማትና ሌሎች የልማት ስራዎች ካሳየችው እድገት በመነሳት የተሞክሮ ማእከል ለማድረግ እየተሰራ ነው ብለዋል።

እየተካሄደ የሚገኘው ሁሉን አቀፍ ልማት ከተማዋን ለኢንዱስትሪ፣ ኮንፈረንስ ቱሪዝም፣ ንግድና ኢንቨስትመንትን ለመሳብ ምቹ ሁኔታ የፈጠረ መሆኑን አብራርተዋል።

ቢሮው በከተማዋ የሚካሄዱ የልማት ስራዎች በጥራትና በፍጥነት እንዲከናወኑ እያደረገ ያለውን ክትትልና ድጋፍ አጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል።


 

የከተማ አስተዳደሩ ምክትል ከንቲባ አቶ አስሜ ብርሌ በበኩላቸው፤ የኮሪደር ልማትን ጨምሮ በከተማዋ እየተገነቡ ያሉ የልማት ስራዎች ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ የሰጡ ናቸው ብለዋል።

የተገኙ ስኬቶችን አጠናክሮ በማስቀጠል በቀጣይ የዲጂታል መሠረተ ልማትን የበለጠ በማስፋፋት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግርን ለመቅረፍ በተሻለ መንገድ እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

በበጀት ዓመቱ የተመዘገቡ ስኬቶች የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ ሥራ ውጤት ናቸው ያሉት ደግሞ  በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የከተማ አስተዳደሩ ከተማና መሰረተ ልማት መምሪያ ስራ አስኪያጅ አቶ ተሻገር አዳሙ ናቸው።

በመጀመሪያውና 2ኛው ዙር ብቻ ስምንት ነጥብ ስድስት ኪሎ ሜትር የኮሪደር ልማት ስራ ማጠናቀቅ መቻሉን ጠቁመው 3ኛው ዙርም በመጠናቀቅ ላይ እንደሚገኝ አረጋግጠዋል።

የተቀናጀ የኮሪደር ልማት ሥራዎችን በማፋጠን የባሕርዳር ከተማን ሁለንተናዊ ተመራጭነት በተጨባጭ የማረጋገጥ ጉዳይ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

በ2019 በጀት ዓመት የታቀዱ የልማት ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት በማከናወን የከተማዋን ህዝብ ተጠቃሚ ለማደረግ በቅንጅት እንደሚሰራ አስገንዝበዋል።

በመድረኩ  የክልሉና የከተማ አስተዳደሩ አመራሮች፣ ባለሙያዎችና ሌሎች ባለድርሻ አካላተ ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም