በአሪ ዞን የመኸር አዝመራን ስኬታማ ለማድረግ የግብአት አቅርቦትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እየተሰራ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በአሪ ዞን የመኸር አዝመራን ስኬታማ ለማድረግ የግብአት አቅርቦትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እየተሰራ ነው
ጂንካ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ በአሪ ዞን የመኸር አዝመራን ስኬታማ ለማድረግ የግብአት አቅርቦትና ቴክኖሎጂ አጠቃቀም ላይ እየተሰራ መሆኑን የዞኑ አስተዳደር ገለጸ ።
በዞኑ የ2018/19 የመኸር አዝመራ የማስጀመሪያ መርሃ- ግብር እየተካሄደ ነው።
የአሪ ዞን ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ገረመው ኃይለማርያም በዚሁ ወቅት እንዳሉት የግብርና ዘርፉን በማዘመን የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እና የስራ እድል ፈጠራን ለማስፋት እየተሰራ ነው ።
በዞኑ የግብርና ምርታማነትን ለማሳደግ የተሻለ የግብአት አቅርቦት እንዲኖር ከማድረግ ባለፈ የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማጎልበት ሞዴል አርሶ አደሮችን ለማፍራት እየተቻለ መሆኑን ገልጸዋል።
በተለይ በበጋው ወራት የተከናወኑ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራዎች የመኸር አዝመራውን ውጤታማ ለማድረግ መደላድል ፈጥረዋል ነው ያሉት።
የአሪ ዞን ግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ ጉራልቅ ይዥማልቅ በበኩላቸው፤ በዞኑ የአየር ንብረት ለውጥ ተፅእኖን የሚቋቋም ግብርናን እውን በማድረግ ምርታማነትን ለማሳደግ እየተሰራ ነው ብለዋል።
ለዚህም የተቀናጀ የአፈርና ውሃ ጥበቃን ጨምሮ የአረንጓዴ ልማት ስራዎች በተለየ ትኩረት እየተከናወነ እንደሚገኝ ገልጸዋል።
ግብርናን ከዝናብ ጥገኝነት በማላቀቅ በመስኖ ልማት ላይ ትኩረት ለማድረግም የገፀ ምድርና የከርሰ ምድር የውሃ አማራጮች ጥቅም ላይ መዋላቸውን አስረድተዋል።
የመኸር አዝመራውን በታቀደው ልክ ስኬታማ ለማድረግም አርሶ አደሮች የግብርና ባለሙያዎችን ምክር በመቀበል፣ የተሻሻሉ ዝርያና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በመርሃ ግብሩ ላይ ከጂንካ ዩኒቨርስቲ ፣ከደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ምርምር ኢንስቲትዩት ፣ከጂንካ ግብርና ምርምር ማዕከል እና የአጋር ድርጅት ኃላፊዎች ተገኝተዋል።