ቀጥታ፡

የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል ነው 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ቴሌኮም ቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የመሪነት ሚና መወጣት የሚያስችል መሆኑን የተቋሙ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬሕይወት ታምሩ ገለጹ። 

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ የተቋሙን  የ2018 በጀት ዓመት እና የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ አፈፃፀም አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ በሰጡት መግለጫ፣ ኢትዮ ቴሌኮም ባለፉት ሰባት ዓመታት ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በትጋት ሲሰራ መቆየቱን ገልጸዋል። 

ኢትዮ ቴሌኮም በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 215 ነጥብ 8 ቢሊዮን ብር ገቢ በማግኘት የእቅዱን 99 ነጥብ 7 በመቶ ማሳካቱንም ገልጸዋል።

ይህ ገቢ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ33 ነጥብ 2 በመቶ እድገት ያሳየ ነው ብለዋል።

በአሁኑ ወቅት የቴሌብር ተጠቃሚዎች ቁጥር 60 ነጥብ 5 ሚሊዮን መድረሱን አስታውቀዋል ።

ባለፈው ዓመት የተጀመረውና ለሶስት ዓመታት የሚተገበረው የቀጣዩ አድማስ ስትራቴጂ ሁለንተናዊ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ እድገትን ለማፋጠን ያለመ መሆኑን አስገንዝበዋል።

ስትራቴጂው ተቋሙ በአፍሪካ የዲጂታል ኢኮኖሚ ውስጥ የድርሻውን እንዲወጣ የሚያስችልና ለአፍሪካ አጀንዳ 2063 ብሎም ለዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 መሳካት ጠንካራ መሰረት የሚጥል መሆኑንም ተናግረዋል።

በስትራቴጂው የአንድ ዓመት አፈፃፀም በርካታ የኔትወርክ ተደራሽነት እና የማዘመን ስራዎች መከናወናቸውን አብራርተዋል።

በዚህም 603 አዳዲስ የሞባይል ጣቢያዎች ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ገልጸው፣ ይህም አጠቃላይ የሞባይል ጣቢያዎችን ቁጥር 10 ሺህ 613 ማድረሱን ተናግረዋል።

በ195 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች መገንባታቸውንም በዚህም 117 ወረዳዎች ተደራሽ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ይህም ተደራሽነትን ማስፋትና አካታችነትን ማረጋገጥ ማስቻሉን ነው ዋና ስራ አስፈፃሚዋ የገለፁት። 

በ195 የገጠር ሞባይል ጣቢያዎች በመገንባታቸው 117 ወረዳዎች ላይ የኔትወርክ ተደራሽነትን በማስፋት አካታችነትን ማረጋገጥ ያስቻለ ትልቅ ስኬት መሆኑን ተናግረዋል።

በበጀት ዓመቱ 264 ከተሞች የአራተኛው ትውልድ (4ጂ) ኔትወርክ አገልግሎት ማግኘት መቻላቸውን ተናግረዋል።

ሰባት ተጨማሪ ከተሞች የ5ጂ አገልግሎት ማግኘታቸውን ተከትሎም፣ የ5ጂ ተጠቃሚ ከተሞች ቁጥርም 33 መድረሱን አስታውቀዋል።

በአጠቃላይ ሁለንተናዊ የቴክኖሎጂ እና የመሠረተ ልማት ማስፋፊያ ስራዎችን መሠረት በማድረግ፣ የኢትዮ ቴሌኮም አጠቃላይ የደንበኞች ቁጥር 90 ነጥብ 1 ሚሊዮን መድረሱን ዋና ሥራ አስፈፃሚዋ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም