በጅማ ዞን ከ1 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን ከ1 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት ተሸጋግረዋል
ጅማ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ በ2018 በጀት ዓመት በጅማ ዞን ከ1 ሺህ 600 በላይ አርሶ አደሮች ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን የዞኑ ኢንቨስትመንትና ኢንዱስትሪ ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ ወይዘሮ ዘሊካ ቡላ ለኢዜአ እንደተናገሩት፤ በዞኑ ለኢንቨስትመንት ያለውን አቅም ወደ ልማት ለመቀየር የአሠራርና የሕግ ማዕቀፎች ተዘርግተዋል።
በዚህም በበጀት ዓመቱ በግብርና፣ አነስተኛና ጥቃቅን ኢንተርፕራይዞችና በኅብረት ሥራ ማኅበራት ተሰማርተው የነበሩ 1 ሺህ 739 አልሚዎች ሀብት አፍርተው ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
ባለሀብቶቹ ወደ ኢንቨስትመንት የተሸጋገሩት 5 ነጥብ 4 ቢሊዮን ብር ካፒታል በማስመዝገብ መሆኑን ጠቁመዋል።
አልሚዎቹ በተሰማሩበት ዘርፍ ውጤታማ ሆነው ወደ ኢንቨስትመንት እንዲሸጋገሩ በመንግሥት 8 ሺህ 27 ሄክታር መሬት የቀረበ ሲሆን፣ 120 ሚሊዮን ብር ብድር መሰጠቱን ገልጸዋል።
ፕሮጀክቶቹ ሙሉ በሙሉ ወደ ሥራ ሲገቡም ከ22 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚና ጊዜያዊ የሥራ ዕድል ይፈጥራሉ ብለዋል።
በዞኑ 2 ሺህ 495 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በሥራ ላይ እንደሚገኙ ጠቅሰው እነዚህ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ከ55 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች በቋሚነትና በጊዜያዊነት የሥራ ዕድል መፍጠራቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ በዴዶ ወረዳ ነዋሪ የሆኑት ጃፈር አብዱልቃድር፤ በ2012 ዓ.ም ተደራጅተው በ50 ሺህ ብር መነሻ ካፒታል በግብርና ሥራ ላይ ተሰማርተው እየሠሩ እንደነበር ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅት ካፒታላቸውን በማሳደግና ትርፋማ በመሆን ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገራቸውን ገልጸዋል።
ማኅበራቸው ከ60 በላይ ለሚሆኑ ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩን ጠቅሰው፣ በቀጣይም ሥራውን በማስፋት በርካታ ወጣቶችን የሥራ ዕድል ተጠቃሚ ለማድረግ አቅደው እየሠሩ እንደሚገኙ አንሥተዋል።
ወጣት ሚሊዮን ዳመነ በበኩሉ፤ በመንግሥት በተመቻቸላቸው የብድር አገልግሎት በሕንፃ ግንባታ ዘርፍ በማኅበር ተደራጅተው በመሥራት ካፒታላቸውን በማሳደግ ወደ ኢንቨስትመንት መሸጋገር መቻላቸውን ተናግሯል።
በኢንቨስትመንት ለመሰማራት ዞኑ ምቹ እና በርካታ አማራጮች ያለው ከመሆኑም ባሻገር መንግሥት የሚያደርግላቸው ድጋፍ እና ክትትል የበለጠ ለመሥራት ተነሣሽነትን እንደፈጠረላቸው አስታውቋል።
በዞኑ በቀጣይ የኢንቨስትመንት ቅበላ አቅምን ለማሳደግ እየተሠራ መሆኑም ተጠቅሷል።