ቀጥታ፡

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የሀገሪቱን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠን ረገድ አበረታች ውጤቶችን አስመዝግቧል 

አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ75 ዓመታት ጉዞው የሀገሪቱን የልማት ምሰሶ በመደገፍ፣ የኢኮኖሚ ዕድገትን በማፋጠንና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገቡን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቦርድ ሰብሳቢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡     

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የተመሰረተበትን 75ኛ ዓመት የአልማዝ ኢዮቤልዩ በዓሉን በተለያዩ መርሃ ግብሮች ማክበር ጀምሯል።  


 

በበዓሉ ላይ የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስትር ወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥና የተቋሙ ቦርድ ሰብሳቢ ኢዮብ ተካልኝ (ዶ/ር) እንዲሁም ጥሪ የተደረገላቸው ከፍተኛ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ የቀድሞ የተቋሙ አመራሮችና ሠራተኞች ተገኝተዋል። 

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እና የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር የቦርድ ሰብሳቢ ዶ/ር ኢዮብ ተካልኝ በዚሁ ወቅት፣ ሕብረተሰቡ በበጋም ሆነ በክረምት አገልግሎት የሚሰጥ መንገድ ለማግኘት ይጓዝ የነበረው አማካይ ርቀት ከ21 ኪሎ ሜትር ወደ 4 ነጥብ 4 ኪሎ ሜትር ዝቅ ማለቱን ገልጸዋል። 

ይህ አፈጻጸም የመንገድ ተደራሽነት ምጣኔውን በአምስት እጥፍ ያሻሻለ ትልቅ ስኬት መሆኑን ጠቁመዋል። 

በቅርብ ዓመታት ውስጥ 44 ሺህ በላይ ኪሎ ሜትር መንገድ መገንባቱን ጠቅሰው ይህም የሀገሪቱን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ እና የሕዝቦችን ማኅበራዊ መስተጋብር በከፍተኛ ደረጃ ማጠናከሩን ተናግረዋል፡፡ 

በተጨማሪም የሀገር ውስጥ ኮንትራክተሮችን አቅም ማሳደግ፣ በቴክኖሎጂ የተደገፉ አሠራሮችን ማስፋፋት እና የአካባቢ ጥበቃን ያገናዘበ ግንባታዎችን ከማካሄድ አኳያም ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል፡፡

ተቋሙ ላለፉት 75 ዓመታት የሀገሪቱን የልማት ምሰሶ በመደገፍ፣ የኢኮኖሚ እድገትን በማፋጠንና ማኅበራዊ ትስስርን በማጠናከር ረገድ አበረታች ስራዎችን ሰርቷል ብለዋል፡፡  

የኢትዮጵያ መንገዶች አስተዳደር በ75 ዓመታት ጉዞው ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር፣ አሠራር እና ትውልድ ተሻጋሪ እውቀት የገነባ አንጋፋ ተቋም መሆኑንም ጠቅሰዋል። 

የአስተዳደሩ ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር መሐመድ አብዱራህማን፣ የመንገድ መሠረተ ልማት ግንባታ ሕዝቦችን የሚያቀራርብ፣ ገበያን የሚያስፋፋና የሀገር አንድነት መሠረትን የሚያጠናክር መሆኑንም ተናግረዋል፡፡


 

የመንገድ አውታሩ መስፋፋት የገበሬውን ምርት ወደ ገበያ፣ ተማሪዎችን ወደ ትምህርት ቤት፣ ህሙማንን ደግሞ ወደ ሕክምና ተቋማት በቀላሉ ለማድረስና የኢንቨስትመንት ፍሰቱን ለማፋጠን መሠረታዊ ኃይል ሆኗል ሲሉም አክለዋል። 

ተቋሙ ከግንባታ ሥራዎች ጎን ለጎን የሀገር ውስጥ የመሐንዲስነት አቅምን በማጠናከር፣ የፕሮጀክት አስተዳደር ሥርዓቶችን በማዘመንና ዲጂታል ቴክኖሎጂዎችን አሠራር ውስጥ በማስገባት ተቋማዊ ብቃቱን ከፍ ማድረጉን ተናግረዋል። 

ለተቋሙ ስኬት መሠረት ለጣሉ የቀድሞ አመራሮችና በአስቸጋሪ መልክዓ ምድራዊ ሁኔታዎችና አየር ንብረት ውስጥ በመስክ ላይ ተሰማርተው መሠረተ ልማቱን ለገነቡ መሐንዲሶች፣ ቴክኒሻኖችና የመስክ ሠራተኞች ምስጋና አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም