የአፍሪካን ዕድገት ለማሳለጥ በታማኝ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፍ ያስፈልጋል - ኢዜአ አማርኛ
የአፍሪካን ዕድገት ለማሳለጥ በታማኝ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፍ ያስፈልጋል
አዲስ አበባ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ የአፍሪካን ፈጣን ዕድገት ለማሳለጥ በታማኝ መረጃና ማስረጃ ላይ የተመሰረተ የፖሊሲ ውሳኔ ማሳለፍ እንደሚያስፈልግ የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) ገለጹ።
ለሁለት ቀናት የሚቆየው 14ኛው የአፍሪካ የፖሊሲ ጥናት ጉባኤ "ፖሊሲን በፈጠራ፣ አካታችና ግልጽ ማስረጃ ማጠናከር" በሚል መሪ ሐሳብ በአዲስ አበባ መካሄድ ጀምሯል።
በአህጉራዊ ጉባኤው ምሁራን፣ ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎችና የልማት አጋሮች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
ሚኒስትር ፍፁም አሰፋ (ዶ/ር) እንደገለጹት፣ የአፍሪካ የቴክኖሎጂ ለውጥ፣ የአየር ንብረት ጫና፣ የሕዝብ ቁጥር ዕድገትና የኢኮኖሚ ተግዳሮትን ለመቋቋም ታማኝና ጥራት ባለው መረጃ ላይ የተመሠረቱ የፖሊሲ ውሳኔዎችን ይጠይቃሉ።
ኢትዮጵያም በመረጃ የተደገፈ የፖሊሲ ውሳኔ አሰጣጥን ለማጠናከር ባለ ስምንት አምድ ብሔራዊ የስታትስቲክስ ልማት ፕሮግራም ይፋ በማድረግ ወደ ሥራ መግባቷን ገልጸዋል።
የብሔራዊ ስታትስቲክስ ሥርዓትን በዘመናዊ የዲጂታል አሠራር በማሸጋገር የግብርናና የኢኮኖሚ ተቋማት ቆጠራ፣ የሕዝብና ጤና ዳሰሳ እንዲሁም የቤተሰብ ደህንነት ዳሰሳዎች መካሄዳቸውን ተናግረዋል።
የጥናት ውጤቶችና መረጃዎችን ከመሰነድ ባሻገር ወደ የበጀት ውሳኔዎችና የመንግሥት ፕሮግራሞች ተግባራዊ እርምጃ ሊቀየሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
በተጨማሪም እንደ የሰው ሠራሽ ዕውቀትና የሳተላይት መረጃ ያሉ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎችን ሲጠቀሙ የግል መረጃ ጥበቃን የሥነ-ምግባር መርሆችንና የሕዝብን እምነት መጠበቅ ወሳኝ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል።
የፖሊሲ ጥናት ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ፈቃዱ ፀጋ በበኩላቸው፣ ምርምርና ጥናት ከፖሊሲ ሂደት ተነጥሎ በሪፖርት ብቻ መቅረት የሌለበት ወሳኝ ጉዳይ ነው ብለዋል።
ተመራማሪዎችና ፖሊሲ አውጪዎች በቅርበት በመሥራት የጥናት ውጤቶችን ወደ ተግባራዊ የፖሊሲ ውሳኔዎች እንዲለወጡም ግፊት ማድረግ እንደሚኖርባቸው ጠቁመዋል።
የአፍሪካን የኢኮኖሚ ሽግግር፣ የአየር ንብረት ለውጥ፣ የትምህርትና የቴክኖሎጂ ተግዳሮቶች ለመፍታት ዕውቀት፣ ፈጠራና ትብብር ወሳኝ መሆናቸውን ገልጸዋል።
የአፍሪካ የተፅዕኖ ግምገማ ተመራማሪዎች ኔትወርክ ሊቀመንበር ፕሮፌሰር አሞስ ንጁጉና፤ ለአህጉሪቱ የልማት ውጤታማነት ተመራማሪዎች፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ መንግሥታትና የልማት አጋሮች በትብብር መሥራት እንዳለባቸው ተናግረዋል።
የጥናት ውጤቶች በጥናት መድረኮች ብቻ ሳይወሰኑ ወደ ውሳኔ ሰጪዎች በመድረስ ለሕዝብ ፖሊሲዎችና ለልማት ውሳኔዎች ቀጥተኛ ግብዓት ሊሆኑ እንደሚገባም አመልክተዋል።