በምሥራቅ ሸዋ ዞን የቡና ልማትን ለማላመድና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በምሥራቅ ሸዋ ዞን የቡና ልማትን ለማላመድና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ነው
አዳማ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦በኦሮሚያ ክልል ምሥራቅ ሸዋ ዞን የቡና ልማትን ለማላመድና ለማስፋፋት የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የዞኑ ግብርና ጽሕፈት ቤት አስታወቀ።
የጽሕፈት ቤቱ ምክትል ኃላፊ አቶ አብነት ዘገየ ለኢዜአ እንዳስታወቁት፣ በክልሉ ከሚገኙ ዞኖች መካከል ምሥራቅ ሸዋ ዞን ቀደም ሲል በቡና ልማት የማይታወቅ ነበር።
ይህንን ሁኔታ ለመቀየርም የዞኑ አስተዳደርና ግብርና ጽሕፈት ቤት በቁርጠኝነት እየሠሩ እንደሚገኙ ገልጸዋል።
በዚህ ረገድ የመጣ የተሻሻለ የቡና ዝርያ በዞኑ በሚገኙ ሁለት የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች እየተዘጋጀ መሆኑን ጠቅሰው፣ እስካሁንም 800 ሺህ የቡና ችግኞች ለተከላ መዘጋጀታቸውን አብራርተዋል።
የቡና ልማቱን በአጠቃላይ በግብርና ኢኒሼቲቭ መሠረት ለማስፋፋት ታቅዶ እየተሠራ መሆኑንም አቶ አብነት አመላክተዋል።
አዳማ፣ ሉሜ፣ ቦራ፣ አዳሚ ቱሉ፣ ዱግዳ እና መተሐራ አካባቢ በተመረጡ ቦታዎች የቡና ልማቱን ለማላመድና ለማስፋፋት ሰፊ ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት በልማቱ የሚሳተፉ አርሶ አደሮች ልየታ ተደርጎ፣ የቡና ችግኝ መትከያ ጉድጓዶች በሳይንሳዊ ዘዴ በየደረጃው እየተዘጋጁ እንደሆነ ገልጸዋል።
በዚህም ለመጀመሪያ ጊዜ በዞኑ 200 ሄክታር አዲስ መሬት በቡና እንደሚሸፈን አመልክተዋል።
ከዚህ ቀደም የቡና ተክል በተበታተነ መልኩ ይተከል ከነበረበት አሠራር በመውጣት፣ በአዲስ ኢኒሼቲቭ በአንድ መንደር (በኩታገጠም) ለማልማት ታቅዶ በልዩ ትኩረት እየተከናወነ መሆኑን ገልጸዋል።
አካባቢው ለቡና ልማት ምቹ ሥነ-ምህዳር እንዳለው የጠቀሱት አቶ አብነት፣ አርሶ አደሮች ይህንን በመገንዘብ የቡና ልማትን ከሌሎች ሰብሎች ጎን ለጎን እንዲያካሂዱ ጥሪ አቅርበዋል።
ጽሕፈት ቤቱም የተሻሻሉ የቡና ችግኝ ዝርያዎችን ከማቅረብ ጀምሮ አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደሚያደርግ አረጋግጠዋል።