ቀጥታ፡

በዞኑ 487 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኖ እየለማ ነው 

ገንዳውኃ፤ ሐምሌ 16/2018(ኢዜአ)፦ በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸር ወቅቱ እስካሁን 487 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኖ እየለማ መሆኑን የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።

የመምሪያው ምክትል ኃላፊ አቶ ጤናው ፋንታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ በ2018/19 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ለሰብል  ልማቱ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ ነው።


 

​በምርት ወቅቱ ከ529 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት  ከ12 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል በላይ ምርት ለመሰብሰብ  ታቅዶ ተግባራዊ እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

እስካሁን  በተደረገ ጥረት 487 ሺህ ሄክታር መሬት በተለያዩ ሰብሎች ዘር ተሸፍኖ እየለማ መሆኑን ጠቁመው ከዚህ ውስጥ  ከ370 ሺህ ሄክታር በላዩ በትራክተር ታርሶ የተዘራ መሆኑን ተናግረዋል።

እንዲሁም  ከ250 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በኩታ ገጠም የለማ መሆኑን አመልክተዋል።

 ከተዘሩ ሰብሎች ውስጥም ገበያ ተኮር የሆኑ ሰሊጥ፣ አኩሪ አተር፣ ጥጥ፣ ቦሎቄና ሌሎች እንደሚገኙበት ጠቅሰዋል።


 

በምርት ወቅቱ ለወጭ ንግድ፣ ለኢንዱስትሪ ግብአትና ለአካባቢ ገበያ የሚሆኑ ሰብሎችም በስፋት እንደሚለሙ ተናግረዋል።

በዞኑ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት አሊ መሐመድ ፤ 60 ሄክታር መሬታቸውን በሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ሌሎች ሰብሎች በዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል። 

መሬታቸውን በትራክተር  ደጋግመው በማረስ በመዝራታቸው ድካምና ወጪ የቀነሰላቸው መሆኑን ተናግረዋል።

አርሶ አደር ደጀኔ ታደሰ በበኩላቸው፤ ኩታገጠም ማሳቸውን በሰሊጥ፣ አኩሪ አተርና ማሽላ ዘር መሸፈናቸውን ገልጸዋል።

በዞኑ በ2017/18 ምርት ዘመን መኸር ወቅት ከ510 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በተለያዩ ሰብሎች በማልማት 10 ነጥብ 5 ሚሊየን ኩንታል ምርት መሰብሰቡን ከመምሪያው የተገኘ መረጃ ያሳያል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም