በሁሉም ዘርፎች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ - ኢዜአ አማርኛ
በሁሉም ዘርፎች የሕዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ ለማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ
አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦በሁሉም ዘርፎች የሕዝቡን ባለቤትነት እና ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ይበልጥ በማረጋገጥ የተጀመሩ ውጤታማ ሥራዎች ተጠናክረው ይቀጥላሉ ሲሉ የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ ገለጹ፡፡
የብልፅግና ፓርት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ አካሂዷል።
የብልፅግና ፓርቲ ምክትል ፕሬዚዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህ በውይይቱ ላይ እንደገለጹት፤ በሁሉም ክልሎች በሁሉም ዘርፎች የተሻሉ አፈፃፀሞችና ዕድገቶች ተመዝግበዋል፡፡
ከሀገሪቷ ከፍተኛ አቅም እና ከህዝቡ ፍላጎት አኳያ አሁንም ብዙ መሰራት እንደሚጠበቅ በአጽንኦት ገልጸዋል።
ህዝቡ በምርጫ ወቅት የሰጠውን ትልቅ እውቅና ያነሱት ምክትል ፕሬዝዳንቱ አቶ አደም፤ አሁን ላይ እንደ አገልግሎት አሰጣጥ፣ የስራ እድል ፈጠራ እና የኑሮ ውድነት ያሉትን አንገብጋቢ ጉዳዮች በቁርጠኝነት መመለስ እንደሚገባ ጠቅሰዋል፡፡
የስራ ዕድል ፈጠራ፣ የገበያ መረጋጋትና የኑሮ ውድነት ቅነሳ ከፍተኛ ትኩረት የተሰጣቸው ጉዳዮች በመሆኑ በሁሉም የአመራር በንቅናቄ መመራታቸውን ተናግረዋል፡፡
ይህም ከዕቅድ አፈጻጸም በሕዝቡ የዕለት ተዕለት ኑሮ ላይ ተጨባጭ ውጤቶች እንዲመዘገቡ ማስቻሉን አመልክተዋል።
ፓርቲው ስራዎችን በህዝብ ንቅናቄ በመምራት ሰባት ዋና ዋና ፋይዳዎች ለማግኘት አስቦ እየሰራ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም ችግሮችን በየደረጃው ግብረ-ኃይል በማቋቋም እና መሪዎችን ግንባር ቀደም በማድረግ እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ በባለቤትነት መምራት ይገባል ብለዋል።
በሁሉም ዘርፍ የህዝቡን ባለቤትነት እና የተደራጀ ተሳትፎ ማረጋገጥ እንደሚገባም ጠቁመው፤ በተጨማሪም የአስተሳሰብ ፣ የአደረጃጀት፣ የፋይናንስ፣ የግብዓት ማነቆዎችን እና ህገ ወጥ ደላሎችን በመለየት ተጠያቂነትን ማረጋገጥም ይገባል ብለዋል።
በመጨረሻም የንቅናቄ ስራዎችን በሂደት ቋሚና ተቋማዊ በሆነ አሰራር መተካት እንደሚገባም ነው የገለጹት።
የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና ገበያን ለማረጋጋት በማክሮ ኢኮኖሚ ከሚከናወኑ ስራዎች ጎን ለጎን እያንዳንዱ ቀበሌና ወረዳ የራሱን ተጨባጭ ሁኔታ በመጠቀም የምርት አቅርቦትን ማሳደግ፣ የህገወጥ ደላሎችን መረብ መበጣጠስ እና ንግድን በስርዓት መምራት ይኖርበታል ብለዋል፡፡
በተጨማሪም ከውጭ ሀገር ስራ ስምሪት ጋር ተያይዞ የሚሰጡ ስልጠናዎች እና የምዘና ሂደቶች (COC) ከዓለም አቀፍ ገበያ ፍላጎት ጋር እንዲጣጣሙ ማድረግ ይገባልም ብለዋል፡፡