ቀጥታ፡

በቀጣዮቹ አስር ቀናት የተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ ያገኛሉ

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦በቀጣዮቹ አስር ቀናት የተለያዩ የሀገሪቷ ክፍሎች ከቀላል እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት ገለጸ።

ኢንስቲትዩቱ ለኢዜአ በላከው መረጃ መሰረት፣ ከሐምሌ 14 እስከ ሐምሌ 24 ቀን 2018 ዓ.ም ባሉት አስር ቀናት ውስጥ የዝናብ ሁኔታን የሚፈጥሩ ሁኔታዎች የበለጠ እየተጠናከሩ እንደሚሄዱ አሰታወቋል።

በዚህም መሰረት በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን፣ መካከለኛው፣ ሰሜን ምስራቅ እና ምስራቅ የሀገሪቷ ክፍሎች የተሻለ የዝናብ ሥርጭት መጠን  ይኖራቸዋል።

በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብና ሰሜን የሀገራችን አካባቢዎች ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።

በተጨማሪም በመካከለኛው፣ ሰሜን ምስራቅ፣ ምስራቅ እና ደቡብ የሀገሪቷ አካባቢዎች ከቀላል እስከ መካከለኛ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚኖራቸው አሃዛዊ የትንበያ መረጃዎች ያመለክታሉ ብሏል።

በሚቀጥሉት አስር ቀናት የክረምት ዝናብ ተጠቃሚ የሆኑ የሀገሪቱ አብዛኛዎቹ አካባቢዎች  ከመካከለኛ እስከ ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙም ነው ኢንስቲትዩቱ የጠቆመው።

በደቡብ ምዕራብ፣ ምዕራብ፣ ሰሜን ምዕራብ፣ ሰሜን እና በመካከለኛው የሀገሪቷ አካባቢዎች ከባድ መጠን ያለው ዝናብ እንደሚያገኙ ገልጿል።

በተጨማሪም በኤሊ ዳር፣ ዱብቲ፣ ሰመራ፣ ቡሬ፣ አሳይታ፣ ሁንዱፎ፣ ገዋኔ፣ ሚሌ፣ ዳሊፋጊ፣ አይሻ፣ ጉሊና፣ አዋሽ አርባ፣ ባቲ፣ ዶሎ አዶ፣ ዳዋ፣ አሶሶ፣ ጎዴ፣ ቋራ፣ አዋሽ ፈንታሌ፣ ጭፍራ፣ ላሬ፣ መተሀራ እና፣ ላሬ፣ ፉኙዶ አካባቢዎች  ከሚኖረው የቀን ከፍተኛ የፀሀይ ሀይል ጋር ተያይዞ ከፍተኛ ሙቀት ይኖራቸዋል።

ኢንስቲትዩቱ በቀጣይ ቀናት የሚኖረውን መልካም አጋጣሚዎችን ለመጠቀም እና የሚጠበቁ አሉታዊ ተጽዕኖዎችን ለመከላከል የግብርና ሚቲዎሮሎጂ ምክር ሀሳብን ከወዲሁ መተግበር እንደሚያስፈልግ አሳስቧል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም