ቀጥታ፡

ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ሥራዎች ተከናውነዋል

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን በማጠናከር የዜጎችን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ሥራዎች መከናወናቸውን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ሙፈሪያት ካሚል ገለፁ።

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ የውይይት መድረክ በአዲስ አበባ ተካሂዷል። 


 

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የሥራና ክህሎት ሚኒስትር ሙፈሪያት ካሚል በመድረክ ላይ እንደገለጹት፤ ክህሎት መር የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራዎችን በማጠናከር የዜጎች ተጠቃሚነትን ከማረጋገጥ አኳያ ውጤታማ ስራዎች ተከናውነዋል።

በበጀት ዓመቱ የሀገር ውስጥ የሥራ ዕድል፣ የውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት እና የቴክኖሎጂ አማራጮችን በመጠቀም የርቀት ሥራ በትኩረት መሰራቱን አንስተዋል። 

በዚህም መሠረት በሶስቱ ዋና ዋና አማራጮች ለአምስት ነጥብ አራት ሚሊዮን ዜጎች የሥራ ዕድል ለመፍጠር ታቅዶ ከአምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን በላይ ማከናወን መቻሉን አብራርተዋል።

ለዜጎች የተፈጠሩት የስራ እድሎች በግብርና፣ በአገልግሎት፣ በኢንዱስትሪ፣ በውጭ አገር የስራ ስምሪት እና በርቀት የተፈጠሩ መሆናቸውን ጠቁመዋል።

ይህ የተሻለ ውጤት እንዲመዘገብ የፓርቲው ቅርብ አቅጣጫና ድጋፍ እንዲሁም የባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቁመዋል፡፡

በውጭ ሀገር የሥራ ስምሪት ከ 631 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ስምሪት በማመቻቸት ዜጎች ተጠቃሚ መሆናቸውን አመልክተዋል።

ከተለያዩ የአረብ ሀገራት በተጨማሪ ወደ ስድስት የአውሮፓ ሀገራትም ዜጎችን መላክ መጀመሩን ጠቅሰዋል፡፡  


 

ሀገራት እያሳዩ ባሉት ፍላጎት መሠረት ስምምነቶች ተፈራርመው ዜጎች አስፈላጊውን የሙያና የቋንቋ ስልጠና አግኝተው ወደ ሥራ እንዲሰማሩ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። 

የዲጂታል እና የርቀት ሥራ (Remote Work) የዲጂታል ቴክኖሎጂን በመጠቀም በርቀት ሥራ ከ41ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር መቻሉንም አብራርተዋል፡፡

ለዚህም የአምስት ሚሊዮን ኢትዮ-ኮደርስ ኢኒሼቲቭ ጋር የተደረገ ማስተሳሰር ትልቅ አስተዋጽኦ ማበርከቱን ጠቅሰዋል፡፡ 

በተጨማሪም ወደ 70 የሚጠጉ የቴክኒክና ሙያ ማዕከላት የዲጂታላይዜሽን ፕሮግራም እንዲቀርፁ ድጋፍ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም