ቀጥታ፡

በ2018 በጀት ዓመት የምርት አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሻሻል በተከናወኑ ተግባራት አበረታች ውጤቶች ተመዝግበዋል 

አዲስ አበባ፤ሐምሌ 15/2018 (ኢዜአ)፦በ2018 በጀት ዓመት የምርት አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሻሻል ከተከናወኑ ተግባራት እና የገበያ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባል ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) ገለጹ፡፡  

የብልፅግና ፓርቲ የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማ እና የ2019 በጀት ዓመት መሪ ዕቅድ ላይ ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ተጠናቋል። 

በዚህ መድረክ የፓርቲው ምክትል ፕሬዝዳንት እና የዋና ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ አደም ፋራህን ጨምሮ ሚኒስትሮች፣ ሚኒስትር ዴኤታዎች እና የክልል አመራር አባላት ተሳትፈዋል።


 

የብልፅግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ አባልና የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ካሳሁን ጎፌ (ዶ/ር) በመድረኩ ላይ በበጀት ዓመቱ የኑሮ ውድነትን ለማቃለል እና ገበያን ለማረጋጋት በተከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት እንዲሁም በቀጣይ አቅጣጫዎች ላይ ሪፖርት አቅርበዋል።

በቀረበው ሪፖርት መሠረት የምርት አቅርቦትን በዘላቂነት ለማሻሻል ከተከናወኑ ተግባራት መካከል የሌማት ትሩፋት መርሃ ግብር ከፍተኛ አስተዋጽኦ አበርክቷል ብለዋል።

በበጀት ዓመቱ 15 ነጥብ 8 ቢሊዮን ሊትር የወተት ምርት መገኘቱን አመልክተው፤ ይህም ከእቅዱ እኳያ እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።


 

የነዳጅ አቅርቦትን በተመለከተ፤ ከዓለም አቀፍ የነዳጅ መስመር መዛባት እና የሆርሙዝ ሰርጥ መዘጋት ተግዳሮቶች ቢኖሩም ታቀዶ ከነበረው 5 ነጥብ 23 ሚሊዮን ሜትሪክ ኩብ የእቅዱን 91 በመቶ ነዳጅ ማቅረብ መቻሉን ተናግረዋል። 

በሕገ-ወጥ አሰራር እና በከፍተኛ የፍላጎት እድገት ምክንያት በገበያው ላይ ተግዳሮቶችን ለመፍታት ጥብቅ ቁጥጥር እየተደረገ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የገበያ መሰረተ ልማትን በማስፋፋት ረገድ አበረታች ውጤቶች መመዝገባቸውን የገለጹት ሚኒስትሩ፤ ባለፉት ስድስት ወራት ውስጥ በሀገር ደረጃ ከተለዩት 7 ሺህ 628 የአካባቢ ገበያዎች መካከል የ3 ሺህ 670ዎቹ የይዞታ ማረጋገጥ ሥራ ተጠናቋል ብለዋል። 


 

በተጨማሪም 804 አዳዲስ የቅዳሜ እና እሁድ ገበያዎች እንዲሁም 32 ዘመናዊ የገበያ ማዕከላት ተገንብተው አገልግሎት እየሰጡ እንደሚገኙ ጠቁመዋል።

የግብይት ትስስርን ለማጠናከር 1 ሺህ 352 የሸማቾች ህብረት ሥራ ማህበራት በትስስሩ የተሳተፉ ሲሆን፤ ለነዚህ ማህበራት ከ3 ነጥብ 33 ቢሊዮን ብር በላይ የሚሆን የሪቮልቪንግ ፈንድ ድጋፍ መደረጉን አብራርተዋል።

በተከናወኑ የበጎ አድራጎት ተግባራት ከ4 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች የማዕድ ማጋራት ተጠቃሚ የሆኑ ሲሆን፤ ከ20 ሚሊዮን በላይ ተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ እና የምግብ ድጋፍ ማግኘታቸውን ተናግረዋል።

ከገበያ ጋር ተያይዞ ያሉትን ችግሮችን ለመፍታት በተደረገው ጥረት ሕገ-ወጥ ኬላዎችን የማንሳት ሥራ መከናወኑን ጠቁመው፤ ለኑሮ ውድነት መባባስ ምክንያት የሆኑ ችግሮች እየተቃለሉ መምጣታቸውን ገልጸዋል።

በገበያ ቁጥጥር እና ሕግ ማስከበር ተግባራት፤ በሕገ-ወጥ ንግድ በተሰማሩ 347 ሺህ ነጋዴዎች ላይ እርምጃ መወሰዱንም ተናግረዋል።

በነዳጅ በሕገ-ወጥ አሰራር በተሳተፉ 688 አካላት ፣የንግድና ፀጥታ አካላትን ጨምሮ ሕጋዊ እርምጃ የተወሰደ ሲሆን፤ 2 ነጥብ 3 ሚሊዮን ሊትር በላይ ነዳጅ ተወርሶ 781 ሚሊዮን ብር በቅጣት ገቢ መደረጉን ገልጸዋል።  


 

በቀጣይ በ2019 በጀት ዓመት ምርትና አቅርቦትን ማጠናከርን ዋና ትኩረቱ ያደረገ ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ መያዙን ገልጸው፤ በዚህም የሌማት ትሩፋትና የከተማ ግብርና እንቅስቃሴዎችን በልዩ ትኩረት የማስፋት ስራ እንደሚከናወን ጠቁመዋል።

በሁሉም የምርት ዓይነቶች ላይ የ10 በመቶ እድገት ታሳቢ በማድረግ ለመስራት የተያዘ ሲሆን፤ ለሸማቾች ህብረት ስራ ማህበራት ልዩ ድጋፍ በማድረግና የገበያ ትስስርን በማጠናከር የግብይት ስርዓቱን ለማረጋጋት በትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።

የገበያ መሰረተ ልማትን ማስፋፋት ሁለተኛው ዋና የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ እስከ 2019 ዓ.ም ድረስ ሙሉ ለሙሉ የይዞታ ማስከበርና ማረጋገጥ ስራዎችን የማጠናቀቅ እንዲሁም በህብረተሰብ ተሳትፎ ቢያንስ የ500 ገበያዎችን ደረጃ የማሻሻል ስራ ይሰራል ብለዋል።

የእሁድና ቅዳሜ ገበያዎችን ቁጥር ወደ 3 ሺህ 439 ለማድረስ እቅድ መያዙን ጠቁመው፤ በግብይት ሰንሰለቱ ውስጥ ያሉ ፈታኝ ሁኔታዎችን በህግና አሰራር ብቻ ለመፍታት የቁጥጥርና የሬጉላቶሪ አቅምን የማሳደግ ስራ ትኩረት እንደሚሰጠው ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም